‘ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ’ በሚል ስም ከተከፈተ ሀሰተኛ የቴሌግራም ቻናል እንጠንቀቅ!

‘Midroc Investment Group’ በሚል ስም የተከፈተ እና ከ78 ሺህ በላይ ተከታታዮች ያሉት የቴሌግራም ቻናል የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ እንደሚገኝ ተመልክተናል።

ይህ ቻናል “የሚድሮክ ባለቤት ሼህ አላሙዲን በወሰኑት መሰረት ከደንበኞቻችን ጥብቅ ትስስር ለመፍጠር የዘመናችን ተመራጭ የመገናኛ ዘዴ የሆነውን የቴሌግራም ገፅ ከፍተናል፡፡ በመሆኑም ገፃችን ሼር አድርገው ተደራሽ ላደረጉ ደምበኞች ጥሩ ማበረታቸ የሚሆን የመኪና ስጦታ አዘጋጅተናል” የሚል መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን በርካታ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮች እንድናጣራ ጥያቄ አድርሰውናል።

ኢትዮጵያ ቼክ ከሚድሮክ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ያገኘው መረጃ ይህ ቻናልም ሆነ መልዕክቱ የሚድሮክ እንዳልሆነ አረጋግጧል።

“በድርጅታችን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስም የተከፈተና ሊቀመንበራችን ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የመኪና ሽልማት እንደሚሸልሙ የሚገልፁ ተደጋጋሚ የውሸት የቴሌግራም ገጽ እንዳለ ተመልክተናል። ነገር ግን ይህ የቴሌግራም ገጽ የሐሰት እንደሆነና ትክክለኛው የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የቴሌግራም ቻናል https://t.me/midrocinvestmentgroup ሲሆን በቅርብ ጊዜም የተከፈተ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
ይህንንም የሐሰት አካውንት ለቴሌግራም ሪፖርት ያደረግንና ክትትል በማድረግ የምናዘጋ መሆኑን እያስታወቅን በውሸት ከተከፈቱ ገጾችና ከአጭበርባሪዎች ራስዎን ይጠብቁ” የሚል መልስ ከሚድሮክ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሰኢድ መሀመድ አግኝቷል። ትክክለኛ የፌስቡክ ገፁ ደግሞ ይህ እንደሆነ ጠቁመዋል: https://www.facebook.com/midroc.username

የታዋቂ ግለሰቦችና ተቋማትን ስም በመጠቀም በአጭር ጊዜ ብዙ የቴሌግራም ቻናል ተከታዮችን ማፍራት በብዛት የሚታይ ማጭበርበሪያ ዘዴ ቢሆንም በርካቶቻችን ግን መሰል የቴሌግራም ቻነሎችን ስንቀላቀል ይስተዋላል።

ስለዚህ ትክክለኛነታቸዉን ያረጋገጥናቸዉን የማህበራዊ ትስስር ገጾችና አካዉንቶችን ብቻ በመከተል እራሳችንን ከተዛቡና ሀሠተኛ መረጃዎች እናርቅ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::