በናይጄርያው ‘P.M News’ ተዛብቶ የቀረበ ኢትዮጵያ-ተኮር ዘገባ!

‘P.M News’ የተባለ የናይጄሪያ ጋዜጣ ኢትዮጵያ ለጦርነት ለማንቀሳቀስ ስትል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ዘጋች በሚል የዜና ርዕስ ዘገባ መስራቱን ተመልክተናል።

የዜና ርዕሱ በጋዜጣው ድረ-ገጽ እንዲሁም ከ652 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የትዊተር አካውንቱ ላይ የወጣ ሲሆን በጥቂት ሰዐታት ውስጥ 550 ገደማ ግብረ-መልሶችን ከትዊተር ተጠቃሚዎች አግኝቷል።

ኢትዮጵያ ቼክ ጋዜጣው የተጠቀመውን የዜና ርዕስ የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጉዳዩን በተመለከተ ከሰጡት መግለጫ እንዲሁም ጋዜጣው በምንጭነት ከተጠቀመው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘጋባ ጋር ያመሳከረ ሲሆን ተዛብቶ የቀረበ መሆኑን አረጋግጧል።

በተለይም ከዜና ርዕሱ በዘለለ የዘገባውን ይዘት ለማይመለከቱ አንባቢያን የተሳሳተ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ “የትምህርት ማህበረሰቡ ለህልውና ዘመቻው ደጀን እንዲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ዝግ ይሆናል” በማለት የገለጹ ሲሆን በዚህ ወቅትም መምህራን፣ ተማሪዎችና ሰራተኞች፣ ሰብል በመሰብሰብ፣ የዘማች ቤተሰቦችን በመርዳት፣ ደም በመለገስና በሌሎች ተግባራት እንደሚሰማሩ አስታውቀዋል።

ለተማሪዎችም ለሚዘጋው የትምህርት ጊዜ ማካካሻ እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::