በምስሉ ላይ የሚታዩት ጠ/ሚር አብይ አህመድ ናቸዉ?

በርከት ያሉ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች ከታች በምስሉ ላይ የሚታየውን የጦር ሜዳ መነጽርና የመከላከያ ሠራዊትን ዩኒፎርም የለበሰ ግለሰብ የሚታይበትን ፎቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወለጋ በቅርብ ቀናት የተነሱት እንደሆነ በመግለጽ ሲያጋሩ ተመልክተናል።

ፎቶውን ካጋሩት መካከል ፈንቅል ሚዲያ የተባለና ከ77 ሺህ በላይ ከታዮች ያሉት እንዲሁም Ethio Press የተባለ ከ202 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጾች ይገኙበታል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት በፎቶው ላይ የሚታዩት ግለሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አለመሆናቸውን አረጋግጧል።

የጦር ሜዳ መነጽርና የመከላከያ ሠራዊትን ዩኒፎርም ለብሰው በፎቶው ላይ የሚታዩት የቀድሞው የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ ሞሐመድ ሁሴን ሲሆኑ ፎቶውን በመስከረም ወር መጀመሪያ ከ13 ሺህ በላይ ተከታይ ባላው የፌስቡክ ገጻቸው ያጋሩት ነበር።

አቶ ሰይድ የጦር ሜዳ መነጽርና የመከላከያ ሠራዊትን ዩኒፎርም ለብሰው የተነሷቸውና ከሌላ አቅጣጫ የተነሱ ፎቶዎችም በፌስቡክ ገጻቸው ተጋርተዋል።

ተቀናብረው፣ ከዐውድ ውጪ ተወስደው እንዲሁም ተዛብተው የሚቀርቡ መረጃዎችን፣ ምስሎችን ወይም ቪድዮዎችን ባለማጋራት እና ባለመቀበል የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ተባብረን እንከላከል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::