ይህ ምስል በደቡብ ወሎ በሚገኝ መጋዘን ላይ የደረሰ ቃጠሎን ያሳያል?

ይህ ከ77 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ አካውንት በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኝ አንድ ወታደራዊ እና የቁሳቁስ ማከማቻ መጋዝን ላይ ከትናንት በስቲያ የቃጠሎ አደጋ መድረሱን የሚገልጽ መረጃ ከፎቶ ጋር አያይዞ ጋር ለጥፏል። 

ኢትዮጵያ ቼክ የሪቨርስ ኢሜጅ መፈለጊያ መገልገያዎችን በመጠቀም ባደረገው ማጣራት ከላይ በተገለጸው አካውንት የተለጠፈው ፎቶ ቆየት ያለ መሆኑን አረጋግጧል። 

ፎቶው ጥር 05 ቀን 2013 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ የእሳት ቃጠሎ በተከሰተበት ወቅት የተነሳ ነበር። በከተማው 02 ቀበሌ ከቀኑ 10፡30 በደረሰ በዚህ አደጋ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ መድረሱን የደቡብ ወሎ ፖሊስ በወቅቱ ያሳወቀ ሲሆን በኤሌትሪክ ምክንያት ቃጠሎው መነሳቱንም በወቅቱ ጠቁሟል (ሊንክ: https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=2809972462554493&id=1668398713378546)

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያን ያነጋገረ ሲሆን፣ “ምንም የተከሰተ የእሳት ቃጠሎ አልነበረም” የሚል አጭር ምላሽ አግኝቷል። 

ቆየት ያሉ ምስሎችን አሁን እንደተነሱ አድርጎ ማቅረብ፣ ፎቶዎችን ማቀናበር እንዲሁም ከሀገር ውጪ የተነሱ ምስሎችን ሀገር ውስጥ እንደተወሰዱ አርጎ ማቅረብ እየተበራከተ ስለሆነ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ማጣራት ሳያደርጉ ለሌሎች እንዳያጋሩ እንመክራለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::