በኢትዮጵያ ከአምስት ሰዎች አንዱ የአዕምሮ ጤና ችግር አለበት? 

በቅርቡ የአዕምሮ ጤናን የተመለከቱ ዜናዎች በርከት ባሉ የዜና እና የህዝብ ግንኙነት ተቋማት ሽፋን ማግኘታቸውን ተከትሎ የተለያዩ ግር የሚሉ እና ትኩረትን የሚስቡ ቁጥሮችን ተመልክተን ነበር። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ‘በኢትዮጵያ ከአምስት ሰዎች አንዱ የአዕምሮ ጤና ችግር አለበት ተባለ’ የሚል ነው። 

በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና ህመም በዚህ ደረጃ ሊገለጽ ይችላል ወይ የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ኢትዮጵያ ቼክ በኤካ ኮተቤ የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑትን ዶ/ር ዳዊት አሰፋን አነጋግሮ ነበር። 

“ይህን አገላለጽ ትክክል ነው ወይም አይደለም የሚለውን ለመበየን መለኪያዎቻችንን በማያሻማ መልኩ ግልጽ ማድረግ አለብን” ይላሉ ዶ/ር ዳዊት። 

በአጠቃላይ የአዕምሮ ጤና ህመም ተብለው ሊገለጹ የሚችሉ ከ360 በላይ ህመሞች መኖራቸውን የሚገልጹት ዶ/ር ዳዊት፣ በማሕበረሰቡ ውስጥም የአዕምሮ ጤና እክል ፍቺ ላይ የጋራ መግባባት እና አጥጋቢ የሆነ መረዳት የለም ሲሉ ያብራራሉ። 

“አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል እብደት (schizophrenia) የሚባለውን የህመም ዓይነት ብቻ ነው የአዕምሮ ጤና ህመም በሚል የሚረዳው። ይህ እጅግ በጣም የተሳሳተ እይታ ነው። ይህ ዓይነቱ ህመም ከአዕምሮ ህመም አይነቶች አንድ በመቶ የሚሆነውን ብቻ የሚወክል ነው” የሚሉት ዶ/ር ዳዊት ሁሉንም የአዕምሮ ጤና ህመሞች ግምት ውስጥ ካስገባን በኢትዮጵያ ከአምስት ሰዎች አንዱ የአዕምሮ ጤና ችግር አለበት የሚለው አባባል ትክክል ይሆናል ሲሉ አረጋግጠዋል። 

እንደ የስነ-ባህሪይ ችግሮችን፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ድብርት፣ ጭንቀት እና ሌሎችም ህመሞች የአዕምሮ ህመም በሚል መታየት አለባቸው በማለትም ጨምረው አብራርተዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::