የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ “በአማራ ክልል የጀመርነው ህግ የማስከበር ስራ በተሳካ ሁኔታ እየሄደ ነው” በማለት ለኢቢሲ መናገራቸውን የሚገልጽ የስክሪን ቅጂ (screenshot) ትናንት እና ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲጋራ ተመልክተናል። 

የስክሪን ቅጂው ከኢቢሲ የፌስቡክ ገጽ እንደተወሰደ የሚጠቁም ሲሆን የአቶ ሽመልስን ፎቶ፣ ተናገሩት የተባለውን መልዕክት እንዲሁም የኢቢሲ መለያ (logo) የተሰናሰኑበት ምስል በዜናው አካልነት አብሮ ይታያል። 

ኢትዮጵያ ቼክ የስክሪን ቅጂውን ትክክለኛነት ለማወቅ ባደረገው ማጣራት የተባለው መልዕክት በኢቢሲ የፌስቡክ ገጽ ላይ ቀርቦ እንዳልነበር እና በቅንብር ተሰርቶ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተለቀቀ እንደሆነ ማረጋገጥ ችሏል። ለዚህም የስክሪን ቅጅውን ይዘቶች መርምሯል፣ ንጽጽር አካሂዷል እንዲሁም ይዘቶችን በተመለከተ ከኢቢሲ የሳይበር ሚዲያ ክፍል ጋር ተነጋግሯል። 

በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው ስክሪን ቅጂ የተጠቀመው የፎንት አይነት ኢቢሲ በማህበራዊ ሚዲያ ለግንባር-ምስሎች (thumbnail images) ከሚጠቀምበት የፎንት አይነት የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ቼክ በርከት ያሉ የኢቢሲ ግንባር-ምስሎችን የመረመረ ሲሆን ሚዲያው የሚጠቀመው ‘ኖኪያ’ የተባለ የፎንት አይነት በመካከለኛ ድምቀት (medium boldness) መሆኑን አስተውሏል። የኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ክፍልም ለግንባር ምስሎች ኖኪያ ፎንት በመካከለኛ ድምቀት እንደሚጠቀም አረጋግጧል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ሌላ ለንጽጽር የተጠቀመው የዜና አጻጻፍ ይትባህሉን (style) ነው። ኢቢሲ በማህበራዊ ሚዲያ በሚያጋራቸው ዜናዎች በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያለ ከሆነ ከትምህርተ ጥቅሱ በኃላ የተናጋሪውን ማንነት ብቻ እንደሚያስቀምጥ አስተውለናል። በስክሪን ቅጅው ላይ ግን በትምህርተ ጥቅሱና በተናጋሪው ማንነት መካከል “..ሲሉ..” የሚል ያልተለመደ አያያዥ ቃል ገብቷል። የኢቢሲ ሳይበር ክፍል በማህበራዊ ሚዲያ ዐርዕስተ ዜና ሲጽፍ ይህን ጨምሮ ሌሎች አያያዥ ቃላቶችን ከትምህርተ ጥቅሱ በኃላ እንደማይጠቀም አብራርቷል። 

በተጨማሪም በስክሪን ቅጅው ላይ የሚታየው የአቶ ሽመልስ ፎቶ የቆየ ሲሆን ፎቶው የተወሰደው ፕሬዝደንቱ የ2013 ዓ.ምን የኢድ አልፈጥ በዓል ምክንያት በማድረግ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል። 

በመጨረሻም ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተዘዋወሩ ያሉት ሁሉም የስክሪን ቅጂዎች ዜናው ከተለጠፈ 18 ደቂቃ እንደሆነው ይጠቁማሉ። ከዛ ውጪ በሌላ ሰው በሌላ ደቂቃ ላይ የተወሰደ የስሪን ቅጂ አለመኖሩ እንዲሁም በሌሎች ሚዲያዎች ተመሳሳይ መልዕክት አለመተላለፉን ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል። 

ከኢቢሲ የፌስቡክ ገጽ እንደተወሰዱ ተደርገው የሚጋሩ የስክሪን ቅጂዎች እየጨመሩ የመጡ ሲሆን ኢትዮጵያ ቼክ ከዚህ በፊት የማጋለጥ ስራ መስራቱ ይታወቃል። የኢቢሲ የሳይበር ሚዲያ ክፍል ለኢትዮጵያ ቼክ እንደገለጸው በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች መበራከታቸውንና ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ቢያንስ በሳምንት አንድ ሀሰተኛ የስክሪን ቅጅ የሚዲያውን ስም በመጠቀም እንደሚሰራጭ አስረድቷል። 

ሆን ተብለው እና ተቀናብረው የሚለቀቁ ፅሁፎችን፣ ምስሎችን እንዲሁም ቪድዮዎችን ሳናረጋግጥ ባለማጋራት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እንከላከል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::