የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚጫወቱባቸው ክለቦች የተጫዋቾቹን ማንነት እና ብሄር ይጠቁማሉ?

ከ30,000 በላይ ተከታዮች ያሉትና ‘Birhanemeskel Segni’ የሚል ስም ያለው የትዊተር አካውንት በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሮን ከተሸነፈ በሗላ ባሰፈረው መልዕክት ተጫዋቾች የተመረጡባቸውን ክለቦች ስብጥር ለሽንፈቱ በምክንያትነት አስቀምጧል። ከመልዕክቱ ጋርም የተጫዋቾቹን ስብጥር ያሳያል ያለውን የስክሪን ቅጅ አያይዟል።

በዚህ በርካታ ተከታዮች ባሉት የትዊተር አካውንት የተላለፈው መልዕክት የተሳሳተና የተዛባ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

ምክንያት 1:- ተጫዋቾች የሚጫወቱባቸው ክለቦች የተጫዋቾቹን ማንነት፣ ብሄር እንዲሁም ዜግነትን አይገልጽም። በትዊተር አካውንቱ ከተላለፈው መልዕክት ጋር በተያያዘው የስክሪን ቅጅ ላይ የተጠቀሱት ክለቦች ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢ የመጡ እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጨዋቾች በቡድናቸው ወስጥ ማካተታቸውን ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች በተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቁጥራቸውን የሚወስን መመሪያ ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህ ውሳኔ ግን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች አይመለከትም።

በውሳኔውም ፌዴሬሽኑ በ2014 ዓ.ም የውድድር ዘመን በየትኛውም የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ከ3 በላይ የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ማስፈረም እንደማይቻል አስታውቋል። በተጨማሪም በከፍተኛ እና በ1ኛ ሊግ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦች ምንም ዓይነት የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ማስፈረም አይችሉም። እንዲህ ያለው መመሪያ በሌሎች ሀገሮችም የሚተገበር ሲሆን ለሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ዕድል መስጠት በምክንያትነት ይጠቀሳል።

ምክንያት 2:- ብሔራዊ ቡድኑን የወከሉ ተጫዋቾች የተመረጡት ከውስን ክለቦች ብቻ ሳይሆን በርከት ካሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ክለቦች ነው። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ከሆኑ 16 ክለቦች 10ሩ ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋች አስመርጠዋል። እንዲሁም ወልቂጤ ከነማ ለአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን አንድ ተጫዋች አስመርጦ የነበረ ቢሆንም ከአበረታች መድሃኒት ጋር በተገናኘ በፊፋ እገዳ ተጥሎበታል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::