“ጅቡቲ አንድም ወታደር ወይም ወታደራዊ ተሽከርካሪ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አላስጠጋችም”— የጅቡቲ ገዢ ፓርቲ ዋና ፀሀፊ ኢልያስ ዳዋሌህ

“ይህ ሀሰተኛ መረጃ ነው፣ ራሴ አሁን ያለሁት ጅቡቲ ነው”— የጅቡቲ አምባሳደር ሙሀመድ ኢድሪስ ፋራህ ለኢትዮጵያ ቼክ 

ራሺድ አብዲ የተባለ ከ136,000 በላይ የትዊተር ተከታይ ያለው ግለሰብ ጅቡቲ ወታደሮቿን እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እያስጠጋች እንደሆነ መረጃ አጋርቶ ነበር፣ ምክንያት ብሎ ያቀረበው ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘውን ዋናውን መንገድ እና የባቡር መስመር ለመጠበቅ ነው ብሏል። 

ይህን ፅሁፍ ተከትሎ የጅቡቲ ገዢው ፓርቲ ዋና ፀሀፊ ኢልያስ ዳዋሌህ ትዊተር ላይ መረጃው የተሳሳተ እንደሆነ ጠቅሰው ፅፈዋል። 

“ጅቡቲ አንድም ወታደር ወይም ወታደራዊ ተሽከርካሪ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አለማስጠጋቷን ላረጋግጥልህ እችላለሁ። ይህን ለማድረግ የሚያበቃ ስጋት አለ ብለን አናምንም፣ ይህም ሆኖ ግን ቀጠናችን ሰላም፣ መረጋጋት እና ጠቢብነት እንደሚያስፈልገው እናምናለን” ብለዋል። 

ራሺድ አብዲ ጅቡቲ ወታደሮቿን እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እያስጠጋች እንደሆነ ቢፅፍም ይህን የሚያስረዳ እና ሊጣራ ወይም ሊረጋገጥ የሚችል የምስልም ይሁን የቪድዮ ማስረጃ አብሮ አላቀረበም። 

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ተጨማሪ አስተያየት በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር ከሆኑት ሙሀመድ ኢድሪስ ፋራህ ጠይቋል። እርሳቸውም “ይህ ሀሰተኛ መረጃ ነው፣ ራሴ አሁን ያለሁት ጅቡቲ ነው” የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::