ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ተልከው ነው?

“ጎንደር ትዩብ” የተባለ እና ከ186 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ “የአሜሪካ መንግስት በዶ/ር አብይ መንግስትና በኢትዮጵያላይ የጣለውን ማእቀብ በድፕሎማሲ ለመፍታት አሜሪካ ወስናለች” የሚል ጽሁፍ አስነብቧል። ገጹ “መልካም ዜና” በሚል ርዕስ ስር ባሰፈረው ጽሁፍ “አሜሪካ ከዶ/ር አብይ መንግስት ሆነ ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የከፋ ቅራኔ ውስጥ መግባት እንደማትፈልግና ነገሮችን በውይይት ለመፍታት አሜሪካ ሴናተሯን [ወደ] ኢትዮጵያ ልካለች” ይላል።

ጎንደር ትዩብ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከአሜሪካው ሴናተር ጂም ኢንሆፍን ጋር ስለመገናኘታቸው በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ያሰራጩትን መልዕከትም በጽሁፉ አካቷል።

ምንም እንኳን ሴናተር ጂም ኢንሆፍን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቸው እና ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር መገናኘታቸው እውነት ቢሆንም፣ ሴናተሩ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በአሜሪካ መንግስት ተልከው ነው የሚለው የጎንደር ትዩብ ዘገባ የተሳሳተ ነው።

የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት ሴናተር ጂም ኢንሆፍን የኦክላህማን ግዛት በመወከል የአሜሪካ ሴኔት አባል ሲሆኑጠቅላይ ሚንስትር አብይንና መንግስታቸውን እንደሚደግፉበተለያዩ ወቅቶች ባሰሟቸው ንግግሮች ገልጸዋል። ሴናተሩየአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት እና ባለስልጣኖች ላይ የቪዛና የምጣኔ ሀብት ዕቀባ ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በሴኔቱ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ዕቀባውን በግልጽ እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።

ከ14 ደቂቃ በላይ በፈጀው ንግግራቸው “ሽብርተኛ” ሲሉ የጠሩትን ህወኃት ከኢትዮጵያመንግስት ጋር በዕኩል ዓይን መመልከት አግባብ አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል። ሴናተሩ በትዊተር ገጻቸውም ተመሳሳይ ይዘት ያለው መልዕክት ለጥፈው ነበር። ከዚህ ቀደም 19 ጊዜ ወደ ኢትዮጵይያ ጉዞ ማድረጋቸውን የሚናገሩት ሴናተር ጂም ኢንሆፍን ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር በተደጋጋሚ መገናኘታቸውንጠቅሰዋል።

ከሳምንታት በፊት በፕሬዝደንት ባይደን ተልከው ለውይይት ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ሴናተር ክሪስ ኩንስ ናቸው።

ከቀናት በፊት በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ምስክርነታቸውን ለመስጠት የተገኙት የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ረዳት ተጠሪ ሮበርት ጎዲች ሀገራቸው ማዕቀብ ለመጣል ገፊ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች መሻሻል የማያሳዩ ከሆን ተጨማሪ ዕርምጃዎችን ልትወስድ እንደምትችል ማስጠንቀቃቸው ይታወቃል። ረዳት ተጠሪው የመንግስታቸው የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጀፍሪ ፊልትማን በሚቀጥሉትጥቂት ቀናት ወደ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚያቀኑም መግለጻቸው ይታወሳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::