ዛሬ በመስቀል አደባባይ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከአንድ ሚልዮን በላይ ሰው ተገኝቷል? 

አሁን አሁን በመላመት የሚሰጡ የህዝብ ስብስብ መጠንን ወይም የሰው ብዛትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በእጃችን ይገኛሉ። ከእነዚህ የህዝብ ስብስብ ግምት መስጫ (crowd estimate) ማወቂያ መንገዶች መሀል አንዱ እና ዋነኛው ማፕ ቼኪንግ ድረ-ገፅ (mapchecking.com) የተባለው ነው። 

ይህን ካልን ዘንዳ ዛሬ ከ1 ሚሊዮን በላይ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ የሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት በመስቀል አደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ እና ለደጋፊዎች ምስጋና እንደቀረበ በኢቢሲ እንዲሁም በከተማው አስተዳደር ሀላፊዎች ተገልጿል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ማፕ ቼኪንግን በመጠቀም በዚህ ቁጥር ዙርያ ማጣራት አድርጓል። 

በመጀመርያ በስፋት የተመለከትነው በየትኛው ስፍራ ላይ ህዝብ ተሰብስቦ እንደነበር ነው፣ ለዚህም በበርካታ ሚድያዎች ላይ የተለጠፉ ቪድዮዎችን እና ፎቶዎችን አይተናል። በዚህም መሰረት በዛሬው ትልቅ በሚባል በዚህ ሰልፍ ላይ (በምስሉ ላይ በክብ እንደሚታየው) መስቀል አደባባይ የሚገኘው ሙሉው የአስፋልት ስፍራ እንዲሁም ገላጣ ቦታ (በፊት አውቶቡስ መቆሚያ እና ኳስ መጫወቻ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው) በሰልፈኞች ተሞልቶ ነበር፣ የመቀመጫ ስፍራው ግን አገልግሎት ላይ አልዋለም ነበር። ጉግል ማፕ እንዲሁም ማፕ ቼኪንግ እንደሚያሳዩት ይህ ስፍራ 36,900 ስኩዌር ሜትር ግድም ነው። 

ይህን ካጣራን በሗላ በአንድ ስኩዌር ሜትር ምን ያህል ሰው ‘ጥቅጥቅ’ ብሎ ሊይዝ እንደሚችል ነው። በዚህ በተጨናነቀ አሰላል (ምስሉ ላይ ይታያል) በአንድ ስኩዌር ሜትር አምስት ሰው ተጠጋግቶ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። 

በስሌቱ መሰረት ይህ አጠቃላይ ስፍራ በጣም በተጠጋጋ ሰው አሰላል እንኳን ሊይዘው የሚችለው የሰው መጠን 184,500 (መቶ ሰማንያ አራት ሺህ አምስት መቶ) ሰው ገደማ ነው። ስለዚህ ከአንድ ሚልዮን በላይ ሰው ተገኝቶ ነበር የሚለው ቁጥር ተጋኖ የቀረበ እንደነበር መረዳት ይቻላል። 

የማፕ ቼኪንግ ድረ-ገፅ ላይ በመግባት እርስዎም ይሞክሩት።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::