የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አሜሪካውያንን ለመታደግ ወደ አፍጋኒስታን በረራ አድርጓል?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አሜሪካውያንን ለመታደግ ወደ አፍጋኒስታን በረራ አድርጓል? 

‘የኢትዮጵያ አሜሪካውያን እድገት ምክር ቤር (EADC)’ የተባለና ከ8,500 በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር አካውንት አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አሜሪካውያንን ለመታደግ ወደ አፍጋኒስታን በረራ ማድረጉን የሚገልጽ መልዕክት አጋርቷል (https://twitter.com/EA_DevCouncil/status/1428414154080067588?s=19)። መልዕክቱንም በአንድ ቪዲዮ አስደግፎ አውጥቷል። 

ኢትዮጵያ ቼክ የቪዲዮውን ምንጭ ለማወቅ ጥረት ያደረገ ሲሆን ‘The RAGEX’ የተባለ የትዊተር አካውንት ቪዲዮውን ቀደም ብሎ ማጋራቱን ለማወቅ ችሏል (https://twitter.com/theragex/status/1428400382045298698?s=19)። ቀደም ብሎ በተጋራው በዚህ ቪዲዮ ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የተባለ ነገር የለም። 

በቪዲዮው ላይ የሚታየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን “ሮም” የሚል መጠሪያ ያለው መሆኑ በግልጽ የሚነበብ ሲሆን ይህም ‘ET-AWM’ በሚል መጠሪያ የተመዘገበ የአየር መንገዱ ኤርባስ A350-941 አውሮፕላን መሆኑን ያመለክታል። 

ኢትዮጵያ ቼክ የET-AWMን ያለፉት ሰባት ቀናት የበረራ ታሪክ ከFlightradar 24 መተግበሪያ ላይ የተመለከተ ሲሆን በተጠቀሱት ቀናት አውሮፕላኑ ወደ አፍጋኒስታን አለማምራቱን አረጋግጧል። የአውሮፕላኑ የበረራ ታሪክ እንደሚያሳየው አውሮፕላኑ ET8500 የተሰኘ የበረራ ቁጥር በመጠቀም ከአንድ ቀን በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ኳታር አል ኡዲድ አየር ማረፊያ የበረረ ሲሆን ከዛም ከአል ኡዲድ ወደ ዋሽንግተን ዱለስ አውሮፕላን ማረፊያ ማምራቱን ያመለክታል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በተጨማሪም በቪዲዮው የሚታየው የአውሮፕላን ማረፊ አል ኡዲድ መሆኑን የቦታ ጠቋሚ (geolocation) መተግበሪያዎችን በመጠቀም አረጋግጧል። 

ታሊባን የአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡልን ከተቆጣጠረ በኃላ አሜሪካንን ጨምሮ በርከት ያሉ ሀገሮች ዜጎቻቸውን በማስወጣት ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን አል ኡዲድ ከካቡል የተነሱ ብዛት ያላቸውን መንገደኛ የጫኑ የጦር አውሮፕላኖች በማስተናገድ ላይ ይገኛል።  ከአል ኡዲድ የደረሱ መንገደኞች በሲቪል አውሮፕላን ወደ ተለያዩ ሀገሮች እንደሚጓጓዙም ኢትዮጵያ ቼክ ያደረገው የሚዲያ ዳሰሳ ያሳያል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::