ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ አካባቢ የደመና ማበልጽጊያ ቴክኖሎጂን ስራ ላይ አውላለች?

‘Egyptian Local News’ የተባለና ከ3,140 በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር አካውንት በታላቁ የህዳሴ ግድብ አካባቢ ባልተለመደ ሁኔታ ደመና መታየቱን፣ ለዳመናው መፈጠር የደመና ማበልጽጊያ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ውሎ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጽ መልዕክት ለጥፏል።

ይህን የትዊተር አካውንት በምንጭነት በመጠቀም ‘FastMereja.net‘ የተባለና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉትን የፌስቡክ ገጽ “ግብፅ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ ደመና የህዳሴ ግድቡን እንዳላይ ጋርዳብኛለች ስትል ከሰሰች” የሚል መልዕክት ማሰራጨታቸውን ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ቼክ ደመና ማበልጸግን በተመለከተ ባለሙያ በማነጋገርና ጥናቶችን በመፈተሽ ከላይ በተጠቀሱት አካውንቶች የቀረበው መረጃ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጅ ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ኃይለማርያም መረጃው በሁለት ምክንያት ሀሰተኛ መሆኑን ያስረዳሉ።

አንደኛ ከንጹህ ሰማይ ደመና በቴክኖሎጅ አይፈጠርም። አቶ ክንፈ እንደሚያስረዱት “በመጀመሪያ ቁልል ደመና መኖር አለበት። ይህ ቁልል ደመና በቂ የሆነ ውሃ፣ በቂ የሆነ ከከፍታ ሊኖረው ይገባል። እዚያ ውስጥ ኬሚካል በመርጨት ውስጡ ያሉትን የደመና ነጠብጣቦች ወደ ዝናብ ነጠብጣብ ማሳደግ ወይ ደግሞ የበረዶ ውቅሩን ደቀቅ እንዲሉ በማድረግ አደጋ መቀነስ ነው። ይህ ነው ደመና ማበለጽግ ማለት።” ለምሳሌ ይላሉ አቶ ክንፈ “ለምሳሌ ዛሬ አዲስ አበባን ብታየው ብሩህ ነው። እዚህ ላይ ደመና መፍጠር በቴክኖሎጅ አይቻልም። ስለዚህ በህዳሴ ግድብ ላይ ደመና ተፈጥሯል የተባለው ሀሰት ነው።”

ኢትዮጵያ ቼክ የተመለከታቸው የሳይንስ ጥናት ወረቀቶችም እንደሚያረጋግጡት ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጅ ደመናን አይፈጥረም።

የአቶ ክንፈ ሁለተኛ ምክንያት በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጂ የተወሰነ የሀገሬቱን ክፍል ብቻ የሚያካልል መሆኑ ነው። አቶ ክንፈ ለኢትዮጵያ ቼክ እንደገለጹት ቴክኖሎጅው በመተግበር ላይ የሚገኘው ከአዲስ አበባ – ሻውራ – ወልድያ ትሪያንግል ውስጥ ነው። በዚህ ትሪያንግል ውስጥ የሚፈጠርን ደመና የሚከታተል ራዳር ሻውራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ራዳሩ ከዚህ ትሪያንግል ውጭ ያሉ አካባቢዎችን አያካልልም። ይህም የህዳሴው ግድብ የሚገኝበትን አካባቢ አይጨምርም ማለት ነው።

ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጅ በሀሳብ ደረጃ ከመቶ አመት በፊት ብቅ ያለ ሲሆን ባለፉት ሰባ ዓመታት ከአርባ በላይ ሀገሮች ወደ ተግባር ቀይረውታል። ቻይናን፣ እስራኤልንና ኢራንን የመሳሰሉ ሀገሮች ቴክኖሎጅውን በስፋት በመጠቀም የሚታወቁ ሲሆኑ በአፍሪቃም ኒጀር፣ ሞሮኮና ደቡብ አፍሪቃ ቴክኖሎጅውን በመጠቀም ተጠቃሽ ናቸው።

ደመናን ለማበልጸግ ጥቅም ላይ የሚውሎ ከሀምሳ በላይ ዘዴዎች ያሉ ሲሆን በሂደቱም የጨው ዝርያ ያላቸው እንደ ክሎራይድ፣ ሶዲየም፣ ፖታሺየም ወዘተ ያሉ ንጥረ ነገሮች ጥቅም ላይ ይውላሉ። ንጥረ ነገሮችን ወደ ደመናው ለማድረስ አንዳንድ ሀገራት የአውሮፕላን ወይንም የድሮን ርጭት የሚጠቀሙ ሲሆን ሌሎች ከመሬት ወደ ሰማይ የሚወነጨፉ ሮኬቶችን ተግባር ላይ ያውላሉ።

ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጅ ድርቅን ለመቋቋም፣ ዝናብ ቀድሞ እንዲዘንብ ለማድረግ፣ በአየር ብክለት ምክንያት የሚፈጠር ጭጋግን ለማስወገድ ወዘት ጥቅም ላይ ይውላል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት እንደገለጸው በኢትዮጵያ በመተግበር ላይ የሚገኘውን ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጅ ሀሳብ ያመነጩት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ሲሆኖ በሂደቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ፣ የተፋሰስ ባለስልጣን፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎ ማዕከል፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት፣ የኢንፎርሜን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ከግሉ ዘርፍ ድሮን ላይ የሚሰሩ ቡድኖች ተሳታፊ ናቸው። ከበረራ ጋር በተያያዘም የኤፌድሪ አየር ሃይል የጥገና ባለሙያዎችና አብራሪዎች ስለመሳተፋቸውም ተገልጿል።

እንደ ኢኖሼሽንና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር መረጃ በኢትዮጵያ በመተግበር ላይ ለሚገኘው ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጅ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መንግስት ድጋፍ አድርጓል። ኢትዮጵያ ደመና ለማበልጸግ የሶዲየም ክሎራይድ እና የፖታሺየም ክሎራይድ ድብልቅ (ሃይድሮስኮፒክስ) ንጥረ ነገር የምትጠቀም ሲሆን ንጥረ ነገሩን ወደ ደመና ለማድረለማድረስ የኣውሮፕላን ርጭትን ተግባር ላይ ታውላለች። ከዚህ በተጨማሪ ንጥረ ነገሩን ከመሬት ወደ ሰማይ ርጭት ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጅን ወደ ስራ ለማስገባት “የግራውንድ ጄነሬተር” ተከላ በእንጦጦ አካባቢ በመገንባት ላይ መሆኑን ሚንስቴሩ አስታውቋል።

የኤኖቬሽናን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ይህንን ቴክኖሎጅ በረሃማ ቦታዎችን ለማልማት በሰፊው ጥቅም ላይ ለማዋል ወጥናለች።

* ኢትዮጵያ ቼክ የቦቶሜትር መገልገያን ጥቅም ላይ በማዋል ባደረገው ፍተሻ ይህን የተሳሳተ መረጃ ያሰራጨው ‘Egyptian Local News’ የተባለ የትዊተር አካውንት ዝቅተኛ የታማኝነት ደረጃ እንዳለው ተገንዝቧል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::