ሀሰተኛ መረጃን “ሳይቃጠል በቅጠል!” 

ከሰሞኑ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በሆኑት በጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ዙርያ በርካታ መረጃዎች ሲወጡ ነበር። አንዳንዶች በህይወታቸው ላይ አደጋ እንደደረሰ ሲፅፉ ሌሎቹ እንደታሰሩ አስነብበዋል። 

ይህን መረጃ ሲያሰራጩ ከነበሩት መሀል 3 ሚልዮን ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ እንዲሁም በትክክለኛ ሚድያ ተመሳስሎ የተከፈተ ሌላ ገፅ ይገኙበታል። 

በዚህ ሁሉ መሀል እጅግ በርካታ የአጣሩልን ጥያቄዎች ለኢትዮጵያ ቼክ ቀርበው ነው፣ የመረጃ ማጣርያ ዴስኩም ከሚመለከታቸው አካላት መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም፣ አንዳንድ ሀላፊዎችም የሚወጡት መረጃዎች እውነታን ወይም ሀሰትነት በግልፅ ከመግለፅ ተቆጥበው ነበር። 

ዛሬ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የ “እንኳን ደስ ያለን” መልእክት አስተላልፈዋል። ይህም ጄነራል ብርሀኑ ጁላ በአሁን ሰአት ስራቸው ላይ እንደሚገኙ አረጋግጧል፣ የፌስቡክ ገፆቹ ያቀረቧቸው መረጃዎች ግን አሁንም እዛው ገፆቹ ላይ ይገኛሉ። 

እንዲህ አይነት ያልተረጋገጡ ወይም ሀሰተኛ መረጃዎች በተለይ ከፍተኛ ተከታይ ባላቸው የማህበራዊ ሚድያ ገፆች፣ አካውንቶች፣ ቻናሎች እና ድረ-ገፆች ላይ ሲወጡ ተከታትሎ እርምት ወይም የማስተካከያ መረጃ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ ያምናል፣ ለዚህም የሚመለከታቸው የመረጃ ሰጪ አካላት ሁሉ በራቸው ክፍት ሊያረጉ ይገባል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::