ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለጉዞ በሚጠቀሙበት አውሮፕላን ዙርያ በማህበራዊ ሚድያ የተሰራጩ ፅሁፎች እና እውነታው!

አብዛኞቹ የአለማችን መሪዎች ጉዞዎችን ሲያደርጉ የሚጠቀሙባቸው አውሮፕላኖች አሏቸው፣ ከእነዚህ ውስጥም የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶችን እና አጃቢዎቻቸውን የሚያጓጉዘው ቦይንግ 747-200B ወይም በተለምዶ Airforce One የሚባለው አውሮፕላን ስመጥር ነው።

ይህ አሰራር በአፍሪካም የተለመደ ሲሆን የአይቬሪኮስት ፕሬዝደንት አላሳን ዋታራ አስር ፕሬዝደንታዊ አውሮፕላኖች በመግዛት/በማስገዛት ቀዳሚ ናቸው። ከኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ደግሞ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ኬንያ መሪዎቻቸውን  ለማጓጓዝ የተገዙ ወይም የተከራዩ አውሮፕላን አሏቸው።

እንደ ሶማልያ እና ደቡብ ሱዳን ያሉ ሀገራት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመዘገቡ የአየር በረራ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አገልግሎት ያገኛሉ። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ መሪዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ሲጠቀሙ እናስተውላለን።

ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሰሞኑን በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ላይ ግን አንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ቅብ (livery) ለየት ያለ መልክ ያለው አውሮፕላን (የተያያዘው ምስል ላይ ይታያል) በተደጋጋሚ ታይቷል፣ ይህም በጠ/ሚር ቢሮ የማህበራዊ ሚድያ ገፆች ላይ እንዲሁም በተለያዩ በሚድያዎች ላይ ተስተውሏል።

ይህንን ተከትሎ በርካታ መላ ምቶች በተለይ ትዊተር ላይ ሲንሸራሸር ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ቼክ ማረጋገጥ የቻለው ይህ ጠ/ሚር አብይ እና ልኡካቸው ሰሞኑን እየተጠቀመበት የሚገኘው አውሮፕላን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚገኘው Royal Jet የተባለ ድርጅት ንብረት ሲሆን ስሪቱም ቦይንግ 737 አውሮፕላን ነው።

ድርጅቱ መቀመጫውን አቡዳቢ ያደረገ ሲሆን ስምንት ቦይንግ 737-BBJ1 እንዲሁም ሁለት ቦምባርዲየር Global 5000 ዘመናዊ እና ቅንጡ አውሮፕላኖችን በማከራየት ስራውን ያከናውናል። የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂም የዚህ ተመሳሳይ አውሮፕላንን የሚጠቀሙ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም በዚህ አውሮፕላን እንደተጓጓዙ በወቅቱ ከተወሰዱ ምስሎች ማየት ይቻላል።

በዚህ አውሮፕላን ዙርያ በማህበራዊ ሚድያ የሚሰራጩ ሌሎች የተለያዩ መረጃዎች አሉ: አንዳንዶች የወር ኪራይ ሂሳቡን ያስቀምጣሉ፣ ሌሎች የውስጥ ገፅታውን ያሳያል ያሉትን ምስል ያጋራሉ።

መረጃዎቹን ለማጥራት በማሰብ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርበን የነበረ ሲሆን ምላሽ ለማግኘት አልቻልንም።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::