ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚድያ እየተሰራጨ ያለ የተሳሳተ መረጃ! 

ሰኞ እለት በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሃዋ ገላን ወረዳ ውስጥ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በመጀመሪያ ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወሩ ተመልክተናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ መላምቶች ሲቀርቡም ተስተውሏል። 

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባልተለመደ መልኩ በቄለም ወለጋ ዞን፣ ሃዋ ገላን ወረዳ ስለተፈጸመው ግድያ በዕለቱ መረጃ ያጋሩ ቢሆንም ግድያውን በተመለከተ በመጀመሪያ ይፋ ያደረጉት እርሳቸው አለመሆናቸውን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድያውን በተመለከተ በትዊተርና በፌስቡክ ገጾቻቸው መረጃ ከማጋራታቸው ከሰዐታት ቀድም ብሎ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ አክቲቪስቶችን ጨምሮ በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ጉዳዩን የተመለከቱ መረጃዎችን ሲያጋሩ እንደነበር ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።   

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጉዳዩን የተመለከተ መረጃ በትዊተር አካውንታቸው ያጋሩት በኢትዮጵያ ሰዐት አቆጣጠር ሰኞ ከሰዐት በኃላ 12 ሰዐት ከ32 ደቂቃ ሲሆን በፌስቡክ ገጻቸው ደግሞ 12 ሰዐት ከ35 ደቂቃ ነበር። ሆኖም ይህንኑ ተመሳሳይ መረጃ ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሰኞ ከቀኑ 10 ሰዐት ከ11 ደቂቃ ላይ መረጃውን በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጹ አጋርቶት ነበር። በተመሳሳይ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ሰኞ ከቀኑ  12 ሰዐት ከ18 ደቂቃ ላይ ከ71 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገጹ ማጋራቱን ተመልክተናል።  

ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረጃዎን ሰኞ ዕለት ከቀኑ 8 ሰዐት ጀምሮ ሲያጋሩ እንደነበርም አረጋግጠናል። በዚህም መሰረት ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሲሰራጭ የነበረው ይህ መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ማየት ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::