የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቴሌግራም በተባለው የፈጣን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ ማንሳቱ ተሰምቷል!

ፍርድ ቤቱ ከአምስት ቀናት በፊት በቴሌግራም ላይ እገዳ የጣለው ድርጅቱ በሀገሪቱ ፕሬዝደንትና ደጋፊዎቻቸው የሚሰራጩ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በተመለከተ እርምጃ እንዲወስድ ከብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ኮንግረስ፣ ፌዴራል ፖሊስና ምርጫ አስፈጻሚዎች በተደጋጋሚ የቀረበለትን ጥሪ ችላ ብሎታል በሚል ነበር።

ሆኖም ቴሌግራም እገዳ ከተጣለበት በኋላ ምላሽ በመስጠቱ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሽሮታል። የቴሌግራም መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓቬል ድሮቭ ካምፓኒው ከብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተላከለትን ኢሜል “በቸልተኝነት” አለማየቱን ገልጾ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን በተመለከተ ላቀረባቸው አቤቱታዎች ምላሽ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

ቴሌግራም የዋና ስራ አስፈጻሚውን መልዕክት ተከትሎ እርምጃ መውሰድ የጀመረ ሲሆን የብራዚል ፕሬዝደንት የር ቦልሶናሮ የለጠፉትን አንድ መልዕክት አንስቷል፣ እንዲሁም በፕሬዝደንቱ ደጋፊነት የሚታወቅና ሀሠተኛ መረጃን በማሰራጨት የሚወቀስን አንድ ቻናል ዘግቷል።

በተጨማሪም ድርጅቱ በብራዚል ቋሚ ተጠሪ ቀጥሯል፣ በርካታ ተከታይ ያላቸውን የቴሌግራም ቻናሎች የሚከታተሉ ሰራተኞች መድቧል፣ በሀሠተኝነት በተጠረጠሩ መልዕክቶች ላይ ምልክት ማሰቀመጥ ጀምሯል።
ቴሌግራም በብራዚል የወሰደው እርምጃ ያልተለመደ ሲሆን ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን እንዲሁም የጥላቻ መልዕክቶችን በመቆጣጠር ረገድ ተገቢውን ሚና እየተወጣ አየደለም የሚል ቅሬታ ከበርካታ መንግስታትና የሰብዐዊ መብት ተሟጋቾች ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወቃል።

የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ቦልሶናሮና ደጋፊዎቻቸውን በሀሠተኛ መረጃ ስርጭት ጠርጥሮ ማጣራት ማድረግ ከጀመረ ቆየት ያለ ሲሆን የሶሻል ሚዲያ ካምፓኒዎችም የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን በመግታት ረገድ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ በማስገደድ ላይ ይገኛል።

ቴሌግራም በብራዚል ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው ሲሆን እ.አ.አ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ 85 ሚሊዮን ብራዚላውያን መተግበሪያውን በስልካቸው ላይ መጫናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ከደጋፊዎቻቸው ጋር ለመገናኘት ይህንኑ ፈጣን የመልዕክት መለዋወጫ የሚጠቀሙ ሲሆን የቴሌግራም ቻናላቸው ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::