‘ሚድሮክ ኢትዮጵያ ግሩፕ’ በሚል ስም ከተከፈተ ሀሰተኛ የቴሌግራም ቻናል እንጠንቀቅ!

‘Midroc Ethiopia Group’ በሚል ስም የተከፈተ እና ከ80 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የቴሌግራም ቻናል የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ እንደሚገኝ ተመልክተናል።

ይህ ቻናል ተቋሙ የተለያዩ ዉድድሮችን ያዘጋጀና ሽልማት እየሰጠ እንደሆነ በመጻፍ ተከታዮቹ የተለያዩ ተግባራትን እንዲፈጽሙ ይጠይቃል።

በቴሌግራም ቻናሉ ላይ ከሚጻፉ መልክቶች መካከልም “ከታች የሚገኘውን ሊንክ በመንካት የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ፤ ከታች የሚገኘውን ሊንክ በመንካት የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ፤ የቴሌግራም ግሩፕ በመቀላቀል 200 የሚሆኑን ሰዎች ወደ ግሩፑ አድ ያድርጉ” የሚሉና ሌሎችም ይገኙበታል።

ይህን ቴሌግራም ቻነል በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑትን አቶ ሰኢድ መሀመድን አናግሯል።

እርሳቸዉም “ቻናሉ የኛ አይደለም፤ መረጃዉም ፍጹም ሀሰት ነዉ” ብለዋል።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የተቛሙ ትክክለኛ ስም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እንጂ ‘ሚድሮክ ኢትዮጵያ ግሩፕ’ አይደለም።

የታዋቂ ግለሰቦችና ተቋማትን ስም በመጠቀም በአጭር ጊዜ ብዙ የቴሌግራም ቻናል ተከታዮችን ማፍራት በብዛት የሚታይ ማጭበርበሪያ ዘዴ ቢሆንም በርካቶቻችን ግን መሰል የቴሌግራም ቻነሎችን ስንቀላቀል ይስተዋላል።

ስለዚህ ትክክለኛነታቸዉን ያረጋገጥናቸዉን የማህበራዊ ትስስር ገጾችና አካዉንቶችን በመከተል እራሳችንን ከተዛቡና ሀሠተኛ መረጃዎች እናርቅ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::