እሁድ በነበረው የደም ልገሳ መርሐ-ግብር ወቅት የተፈጠረው ምን ነበር?

በአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ወዳጆች፣ አድናቂዎችና ደጋፊዎች የተመሰረተው “ወደ ፍቅር የበጎ አድራጎት ማህበር” ሀምሌ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ሊያደርገው የነበረውን የደም ልገሳ መርሐ-ግብር ‘’መፈጸም አለመቻሉን’’ የሚገልጽ አጭር መግለጫ ካጋራ በኋላ ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑን ተመልክተናል።

ኢትዮጵያ ቼክ የማህበሩን መግለጫ ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰጡ የሚገኙ አስተያየቶችን፣ ቅሬታዎችን እንዲሁም ግራ መጋባቶችን ከተመለከተ በኋላ ስለጉዳዩ ይበልጥ ለመረዳት የወደ ፍቅር በጎ አድራጎት ማህበርን እና የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎትን አነጋግሯል። እንዲሁም በእለቱ በቀጥታ የተሰራጩ ቪዲዮዎችንና ፎቶዎችን ተመልክቷል፣ ተከለከሉ የተባሉ ማስታወቂያዎችንና ባነሮችንም አይቷል።

የወደ ፍቅር በጎ አድራጎት ማህበር ሰብሳቢ አቶ ምስክር ታደሰ ማህበራቸው ባለፉት ስምንት ዓመታት ከኢትዮጵያ ደም ባንክ ጋር በቅርበትና በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ለኢትዮጵያ ቼክ አስገንዝበው በነዚህ ጊዚያትም የማህበሩ አባላት በየሶስት ወሩ እንዲሁም የአርቲስት ቴዎድሮስ የልደት ቀንን አስታኮ አድናቂዎቹ፣ ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ በዓመት አንድ ጊዜ የደም ልገሳ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ የአርቲስቱን የልደት ቀን አስታኮ የሚደረገው የደም ልገሳ መርሐ-ግብር በርካቶች የሚሳተፉበት ሲሆን ባለፈው ዓመት 1,007 ሰዎች ደም የለገሱበት መርሐ-ግብር በሪከርድነት መመዝገቡን አንስተዋል። በዚህም የደም ባንኩ የእውቅና ሰርተፊኬትና ሜዳሊያ መስጠቱን አስታውሰዋል።

በዚህ ዓመትም የደም ልገሳ መርሐ-ግብሩን የበለጠ ለማስፋት ከደም ባንክ ጋር በቅርበት ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ምስክር ባንኩም እስከ ዋዜማው ዕለት ድረስ የስፖንሰርነት ድጋፍ የታከለበት ቀና ትብብር ሲደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።

በዚህም ማህበሩ ላቀደው የደም ልገሳ መርሐ-ግብር በግብዓትነት የሚውሉ 8 የሚሰቀሉ ባነሮችን፣ 7 በቁም የሚተከሉ ማስታወቂያዎችን (rollup ads) እና 1,000 ተለጣፊ ፖስተሮችን የደም ባንኩ ስፖንሰር ሆኖ እንዳሰራላቸው ተናግረዋል።

ሆኖም ግን በደም ልገሳ መርሐ-ግብሩ ዋዜማ ያልጠበቁት ነገር እንደገጠማቸው አቶ ምስክር ለኢትዮጵያ ቼክ ገልጸዋል። በዋዜማው የደም ባንኩ በፌስቡክ ገጹ አጋርቶት የነበረውን የማህበሩን ማስታወቂያ ማንሳቱን እንዲሁም በደም ልገሳው ዕለት የአርቲስት ቴዎድሮስ ምስል የሚታይባቸውን በቁም የሚተከሉ ማስታወቂያዎችን መጠቀም እንደማይችሉ እና በተጨማሪም የደም ልገሳ በሚደረግበት ቦታ የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ ማሰማት እንደማይችሉም እንደተነገራቸው አብራርተዋል። ለዚህም አሳማኝ ምክንያት እንዳልቀረበ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ ተከለከሉ የተባሉትን በቁም የሚተከሉ ማስታወቂያዎች የተመለከተ ሲሆን በማስታወቂያዎቹ ላይ የአርቲስት ቴዎድሮስ ምስሎች እንዲሁም “ወደ ፍቅር”፣ “ሺ ሆነን የሺዎችን ህይዎት እንታደግ”፣ “Find the HERO in U”፣ “መልካም ልደት ለክቡር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን”፣ “እንኳን ደህና መጡ ወደ ፍቅር” የሚሉ ጽሁፎች ይነበቡባቸዋል። በተጨማሪም ማስታወቂያዎችን ስፖንሰር ያደረገው የብሔራዊ ደንም ባንክ ስምና አርማ፤ የመርሐ-ግብሩ አዘጋጅ የወደ ፍቅር ስምና አርማ ተጽፎባቸዋል።

አቶ ምስክር ለወራት ተዘጋጅተንበታል ያሉት መርሐ-ግብር እንዳይስተጓጎል በዕለቱ የማህበሩ አባላት ማልደው ስቴዲየም አካባቢ ወደ ሚገኘው የደም ባንክ መሄዳቸውን ገልጸው ማስታወቂያዎቹንና ባነሮችን መስቀላቸውን ገልጸዋል።

“ሆኖም ማንነታቸውን ያላወቅናቸው ሰዎች በቁም የሚተከሉ ማስታዎቂያዎቹን እንድናነሳ አስገደዱን፣ ምክንያታቸውንና ማን እንዳዘዛቸው አልገለጹልንም” በማለት ለኢትዮጵያ ቼክ አስረድተዋል። ጉዳዩን ለማርገብ ብዙ መጣራቸውን ተናግረው እንዳልተሳካላቸው ገልጸዋል።

ሁለት ሰዐት ይጀመራል በተባለው መርሐ-ግብር ላይ ከደም ባንኩ ባለሙያዎች ውጭ ሃላፊዎች አለመገኘታቸውን ተናግረው በስልክም ለማግኘት ያደረጉት ሙከራም አለመሳካቱን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ ደም ልገሳው እንዳልተደረገ የሚገልጹ መልዕክቶች በማህበራዊ ሚዲያ የተመለከተ ሲሆን በአንጻሩ የቴዲ አፍሮን ምስል ያለበትን ቲሸርት የለበሱ ሰዎች በዕለቱ ደም ሲለግሱ የሚታይባቸው በቀጥታ የተሰራጩ ቪዲዮዎችንና ፎቶዎችን ተከታትሏል።

በቀጥታ ከተሰራጩ ቪዲዮዎች መካከል እሁድ ከቀኑ 6 ሰዐት 31 ደቂቃ ጀምሮ Teddy Afro Fans የሚል ስም ባለውና 324,970 ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገጽ የተጋራ 8 ደቂቃ የሚረዝ ቪዲዮ የሚገኘበት ሲሆን በቪዲዮውም ለአርቲስቱ መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹ ሰዎች ደም ሲለግሱና ከልገሳው በኋላ ፋንታ ሲጠጡ ይታይበታል።

ኢትዮጵያ ቼክ ‘’ደም ልገሳው ተከናወነ ወይስ ቀረ?” ሲል አቶ ምስክርን ጠይቋል። አቶ ምስክር “ማህበራችን ባወጣው መግለጫ ‘የደም ልገሳው ተከልክሏል፣ አልተካሄደም’ አላለም፤ ነገሮች ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ እንዳያመሩ ስናስተባብር ነበር።

ሁለት ሰዐት የተባለው መርሐ-ግብር አራት ሰዐት ላይ ተጀመረ፤ ደም የለገሱ አሉ፤ ቅሬታ ተሰምቷቸው ቆመው የነበሩ ሰዎችም ነበሩ፤ እኛም እስከ ምሽት መደረግ የነበረበትን ከቀኑ ሰባት ሰዐት አካባቢ መርሐግ-ብሩን አቋርጠን ተመልሰናል። የሆነው ቀጥተኛ ክልከላ ሳይሆን ጫና በመፍጠር በተዘዋዋሪ ማስተጓጎል ነበር” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬን አነጋግሯል። አቶ ሀብታሙ “የደም ልገሳ መርሐ-ግብሩ በተያዘለት ፕሮግራም ተከናውኗል።

በዕለቱም 170 ዩኒት ደም ተሰብስቧል። የተከለከለ ነገር አልነበረም። እኔም በቅርበት ስከታተለው ነበር” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።

የአርቲስት ቴዲ አፍሮ ምስል የሚታይባቸው ማስታወቂያዎች ስለመከልከላቸው ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የደም ባንክ አገልግሎቱ የሚመራባቸውን የገለልተኝነት መርሆችን አብራርተው ከኤዲቶሪያል ፖሊሲው ጋር የሚጋጭ ይዘት ያለው ነገር እንደማይፈቀድ ገልጸዋል።

ከማስታወቂያዎች ክልከላ ጋር በተያያዘ “ከበላይ አካል የመጣ ትዕዛዝ ነው የሚባለው ነገርም ትክክል አይደለም” ብለዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::