አባይ ሚድያ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል ለመሆን በዕጩነት በቀረቡት ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ዙርያ ያሰራጨው የተሳሳተ ዘገባ!

አባይ ሚዲያ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል ለመሆን በዕጩነት ከቀረቡ ግለሰቦች መካከል ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ እራሳቸውን ማግለላቸውን የሚገልጽ መረጃ ማሰራጨቱን ተመልክተናል።

መረጃው የተሰራጨው ሚዲያው በየዕለቱ በሚያቀርበው ‘ላምባዲና’ በተሰኘ የውይይት ፕሮግራሙ ላይ ሲሆን ከተወያዮች መካከል አርቲስት አስቴር በዳኔ “ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ… እኔ የዶክተር አብይ ደጋፊ ስለሆንኩ እራሴን አግልያለሁ ብሏል” በማለት ስትናገር ትደመጣለች።

ፕሮግራሙም በአባይ ሚዲያ የዩትዩብ ቻናል “የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል የሆኑት ራሳቸውን አገለሉ!!!” በሚል ርዕስ በምስሉ ላይ እንደሚታየው ተጭኖ ይታያል።

ጉዳዩን በተመለከተ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ማስተባበያ ሰጥተዋል። “አስቴር በዳኔ በአባይ ሚዲያ ቀርባ እኔ የዶ/ር አብይ ደጋፊ ስለሆንኩ እራሴን አግልያለሁ ብሏል ስትል ሰማሁ። የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን 42 እጩዎች ሰሞኑን ይፋ ሆኗል። እኔም አንዱ እጩ መሆኔን ተመልክቻሁ። ለጊዜው ለአጭር ጊዜ ሥራ በሀገር የለሁም። በዚህ ጉዳይ ላይ በየትኛውም ሚዲያ አልተጠየኩም። አልተናገርኩም። ሐሰት ነው። ይሁንና ለዚህ ታላቅ ሀላፊነት በመታጨቴ ክብር ይሰማኛል” ብለዋል።

በአባይ ሚዲያ የተሰራጨውን መረጃ በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ አርቲስት አስቴር በዳኔን ያነጋገረ ሲሆን መረጃውን ከኢትዮ 360 መስማቷል ገልጻለች።

ኢትዮጵያ ቼክ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ በኢትዮ 360 ሚዲያ የተላለፉ ፕሮግራሞችን ተመልክቷል። ጥር 29 ቀን በኢትዮ360 “ዛሬ ምን አለ” ፕሮግራም የፕሮግራሙ አቅራቢዎች ከእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ጋር በተገናኘ ዶክተር በድሉን በምሳሌነት የጠቀሱ ሲሆን አባይ ሚዲያ ካሰራጨው መረጃ ጋር አንድ አለመሆኑን ተመልክተናል።

ከፕሮግራሙ አቅራቢዎች አንዱ የሆነው ሀብታሙ አያሌው በዚህ ፕሮግራም ላይ የተናገረው “ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራም ቢሆን በፍቃደኝነት… እዚህ ላይ አስታሪቂ ሆነህ ግባ ሲባል… እኔ የአብይ ደጋፊ ስለሆንኩኝ በአስታራቂነት ሚና ልጫወት አልችልም” ብለው ከእጩነታቸው በፈቃዳቸው ሊለቁ እንደሚገባ የግል ሀሳቡን አንፀባርቋል (ከ26ኛ ደቂቃ ጀምሮ; https://www.youtube.com/watch?v=ZLtQ9Xsmdwo)

ስለዚህ በአባይ ሚድያ ላይ በአርቲስት አስቴር አማካኝነት የቀረበው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል፣ ምክንያቱም በሀብታሙ አያሌው የቀረበውን የግል አስተያየት እንደ እውነታ በመውሰድ አንድ የተሳሳተ ይዘት ያለው ፕሮግራም ተሰርቶበታል።

ከሳምት በፊት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42 የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮችን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::