የውሳኔ ሀሳቡ እንዲቋረጥ ተወሰነ ወይስ እንዲዘገይ ተደረገ?

“የአሜሪካ ኮንግረስ እና ሴኔት HR6600 እና S3199 ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ እንዲቋረጥ ወሰነ” እንዲሁም “የአሜሪካ ኮንግረስ እና ሴኔት HR6600/ እና S3199 ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ እንዲዘገይ ወሰነ” የሚሉ ሁለት መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ ተመልክተናል።

የመጀመሪያውን መረጃ ካሰራጩት መካከል አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ እና የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የፌስቡክ ገጾች የሚገኙበት ሲሆን ለመረጃው ምንጭ አልጠቀሱም። ሁለተኛው መረጃ በዋናነት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ አሜሪካ ሲቪክ ካውንስልን የትዊተር ገጽ በመረጃ ምንጭነት ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ቼክ የነዚህን መረጃዎች ትክክለኛነት ለማወቅ የሚዲያና የድረ-ገጾች ዳሰሳ ያደረገ ሲሆን ረቂቅ ሕጎቹ እንዲዘገዩ ስምምነት ላይ መደረሱን የሚገልጽ መረጃ በመጀመሪያ ያጋራው ‘ዘ አፍሪካን ሪፖርት’ የተባለ ሚዲያ መሆኑን ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በመረጃ ምንጭነት የጠቀሰው የኢትዮጵያ አሜሪካ ሲቪክ ካውንስልን የትዊተር ገጽም የዘ አፍሪካ ሪፖርት ለመረጃው ዋቢ ማድረጉን ተመልክተናል።

ዘ አፍሪካን ሪፖርት በትናንትናው ዕለት “Congress hits pause on new Ethiopia sanctions as leverage in truce deal” በሚል አርዕስት ባወጣው ዜና ሰብዐዊ እርዳታ ለማቅረብ ሲባል ይፋ የተደረጉት ግጭት የማቆም ስምምነቶች ተግባር ላይ እስከዋሉ ድረስ የኮንግረሱ አባላት ረቂቅ ሕጎችን ለማዘግየት መስማማታቸውን አስነብቧል።

ኢትዮጵያ ቼክ በተጨማሪም የዘ አፍሪካን ሪፖርት ማኔጅንግ ኤዲተር ኒኮላስ ኖርብሩክ “It’s not over until it’s over” በሚል መግቢያ የጻፈውን አጭር መልዕክት የተመለከተ ሲሆን ጦርነቱ የሚያገረሽ ከሆነ እንዲዘገዩ የተደረጉት ረቂቅ ሕጎች እንደገና እንደሚንቀሳቀሱ ከምክርቤቱ አባላት መስማታቸውን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ቼክ የአሜሪካ ኮንግረስንና ሴኔትን እንዲሁም የረቂቅ ሕጎችን ሂደት የሚከታተለውን የGovTrack.us ድረገጾች የተመለከተ ሲሆን HR6600 እና S3199 ረቂቅ ህጎችን ስለመቋረጣቸውም ሆነ ስለመዘግየታቸው የሚገልጽ መረጃ አላገኘም።

በዚህ መሰረት እንዲዘገይ መደረጉን የዘገቡት ትክክለኛ ሲሆኑ እንዲቋረጥ እንደተደረገ የፃፉት ግን የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::