ወ/ሮ ያስሚን ወሃቢረቢ በቁጥጥር ስር ዉለዋል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ ነው!

የአዲስ አበባ ከንቲባ ፅ/ቤት በትናንትናው እለት ሀምሌ 01/ 2014 የወጣውን የ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ “ከባንክ የተላከውና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነቶች ተግኝተዋል… በጉዳዩ የተጠረጠሩ ባለሙያዎች እና አመራር በቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ እየተደረገ ይገኛል” ብሎ ነበር።

ይህንን ተከትሎ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ያስሚን ወሃቢረቢ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በርካታ ፅሁፎች እየተዘዋወሩ ይገኛል።

ነገር ግን በቁጥጥር ስር ውለዋል ከተባሉት ግለሰቦች መካከል ወ/ሮ ያስሚን እንደማይገኙበት እና እንዳልታሰሩ ኢትዮጵያ ቼክ በቀጥታ ከወ/ሮ ያስሚን እና ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

ወ/ሮ ያስሚን መረጃው ትክክል እንዳልሆነ በፅሁፍ መልዕክት ለኢትዮጵያ ቼክ ያሳወቁ ሲሆን ከከተማ አስተዳደሩ የደረሰን መረጃም ይህን ያረጋግጣል። ወ/ሮ ያስሚን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባል ናቸው።

ያልተረጋገጡ፣ ከአውድ ውጭ የሚቀርቡ እና ምንጫቸው ያልተጠቀሰ መረጃዎችን ባለማጋራት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እንከላከል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::