“መረጃዉ ዉሸት ነዉ፣ እንደዚህ ተደርጎ አያዉቅም”— ኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ተሰማ ለኢትዮጵያ ቼክ

በኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ተሰማ ስምና ምስል የተከፈተ ይህ የፌስቡክ ገጽ አልቢትሩ የ2022 ኳታር አለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ለመዳኘት ኢትዮጵያውያን በኦንላይን (online) ድምፅ እንዲሰጧቸዉ ይጠይቃል።

ይህን ከ22 ሰዓታት በፊት የተጻፈ ፅሁፍ በበርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ተጋርቷል፣ በርካቶችም በሃሳብ መስጫ ቦታ (ኮመንት) አማካኝነት ለአልቢትሩ የመልካም ምኞታቸዉን እያስተላለፉ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ይህ ፌስቡክ ገጽ የኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ እንዳልሆነ ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

የፌስቡክ ገጹ የርሳቸዉ እንዳልሆነ ለኢትዮጵያ ቼክ የነገሩት ግለሰቡ እየተጋራ የሚገኘዉ መረጃም ሀሰት መሆኑን ነግረዉናል።

“መረጃዉ ዉሸት ነው፣ እንደዚህ ተደርጎ አያዉቅም። በእግርኳስ ስፖርት አንድ ሰዉ በፐርፎርማንስ (ብቃት) እንጂ በቮት (ድምጽ) ተመርጦ አያዉቅም” ብለዋል።

“እኔን ጫና ዉስጥ ለመክተት ነዉ እንደዚህ የሚያደርጉት። ሆን ብሎ በድምጽ ነዉ ማለት የኔ ዓላማም ህልምም አይደለም” ሲሉም በድርጊቱ ያለመደሰታቸዉን ኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ገልጸዋል።

ነሃሴ 2013 የተከፈተዉ ይህ ገጽ በተለያዩ ጊዜያት ኢንተርናሽናል አልቢትሩን በመምሰል መረጃዎችን ሲያጋራ ቆይቷል።

ለምሳሌ ያክል የ2021 አፍሪካ ዋንጫ በካሜሮን እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ዳኛዉን በመምሰል መረጃዎችንና ምስሎችን ሲያጋራ ነበር።

የዳኛዉ ትክክለኛ ፌስቡክ አካዉንት https://www.facebook.com/bamlak.tessema ሲሆን የትዊተር አካዉንታቸዉ ደግሞ https://twitter.com/bamlaktessema1?s=21 ነዉ።

ትክክለኛ የማሕበራዊ ትስስር ገጾችን ብቻ በመከተል የሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎች ሰለባ እንዳንሆን ራሳችንን እንጠብቅ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::