“ለጊዜው እንደዚህ ያለ መግለጫ አላወጣንም”— የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጌጥዬ ያለው ለኢትዮጵያ ቼክ

በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ስም ወጣ የተባለ ‘መግለጫ’ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲዘዋወር ተመልክተናል። መግለጫው “ፋኖን እና ከትህነግ ጋር የሚደረገውን ድርድር በተመለከተ የባልደራስ አቋም መግለጫ” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ዝርዝሩ በሁለት ገጾች ተካቷል።

መገለጫውን ካጋሩት መካከል ከ234 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ‘KIYYA Hararghe’ የተባለ የፌስቡክ ገጽ ይገኝበታል። ይሁንና ይህ መግለጫ በፓርቲው ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ አልተጋራም።

ኢትዮጵያ ቼክ የመግለጫውን ትክክለኛነት ለማጣራት የደብዳቤውን ይዘት የመረመረ ሲሆን ቅርጹንም ከዚህ በፊት ፓርቲው ያወጣቸው ከነበሩ መግለጫዎች ጋር አነጻጽሯል። በንጽጽሩም ደብዳቤው ቀን፣ ቁጥር፣ ፊርማ፣ ሰማያዊ ማህተም፣ አድራሻ እና ሌሎች ጉድለቶች እንዳሉበት ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ቼክ ስለደብዳቤ ትክክለኛነት በተጨማሪ ለማወቅ የፓርቲውን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጌጥዬ ያለውን ያነጋገረ ሲሆን ደብቤው ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። ሃላፊው “ለጊዜው እንደዚህ ያለ መግለጫ አላወጣንም፤ ፋኖን እና ተያያዥ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ በቅርቡ መግለጫ እናወጣለን” ብለዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::