በምርጫ ጊዜ የተደነገጉ ክልከላዎችን የመጣስ ወንጀል!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 16፣ 2013 ዓ.ም. ባወጣው ማሳሰቢያ ዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የተከለከሉ እና ወንጀል የሆኑ ጣልቃ ገብነቶችን እንደታዘበ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስነብቦ ነበር። 

እነዚህ የመንግስት ሰራተኞች የፓርቲ ወኪልነትን የሚያሳይ መታወቂያ ሳይኖራቸው ስሙ ባልተጠቀሰው የምርጫ ጣቢያ በመገኘት የምርጫ አስፈጻሚዎችን መረጃ እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎች የመራጮች ምዝገባን ለመጎብኘት እና መረጃዎችን ለመውሰድ ጥረት አድርገዋል ሲልም ያስረዳል። 

ነገር ግን ማንኛውም የመንግስት እርከን ሰራተኛ ከቦርዱ የበላይ ሃላፊዎች እውቅና በማግኘት ወይም በልዩ የደህንነት ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር እነዚህ እና መሰል ጣልቃ ገብነቶች ሲፈጽም ከተገኘ በምርጫ ህጉ እና በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እንደሚያስቀጣ ይህ የቦርዱ ማሳሰቢያ ያረጋግጣል። 

የቅጣቶቹን ምንነት እና ክብደት እንዲያብራሩልን የህግ አማካሪ እና ጠበቃ አቶ ኪያ ጸጋዬን ኢትዮጵያ ቼክ አናግሯቸው ነበር። በአሁኑ ወቅት ምርጫ እና የምርጫ ህጎችን በተመለክተ ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኙት አቶ ኪያ፣ “ከምርጫ ጋር የሚያያዙ ማንኛውም ጣልቃ ገብነቶች ወንጀል መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል” ይላሉ። 

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቀጥር 1162/2019 ጠቅሰው “ይህን ወንጀል ሲፈጽም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ከብር 30,000 እስከ ብር 50,000 የገንዘብ መቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማያንስ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ሊቀጣ ይችላል” ሲሉ የቅጣቱን ክብደት ያስረዳሉ፡፡ 

ይህ ብቻ ግን አይደለም ይላሉ አቶ ኪያ። 

“ቦርዱ እንደጥፋቱ ሁኔታ ጉዳዩን ወደ አቃቤ ህግ ሊመራው የሚችል ሲሆን መቀጮውም በዚያው ልክ ከበድ ያለ ይሆናል።” 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማሳሰቢያው የጠቀሳቸው ክልከላዎች፦

1. ማንኛውም የዝቅተኛው መንግስት እርከን ሰራተኛ (ቀበሌ፣ ወረዳ….) ወይም ያልተፈቀደለት ሌላ አካል ምርጫ ጣቢያ ውስጥም ሆነ 200 ሜትር ርቀት ዙሪያ ላይ እንዳይገኝ 

2. ቦርዱ ለፓርቲ ወኪሎች የእውቅና ባጅ በመስጠቱ የእውቅና ባጅ ከተሰጣቸው ፓርቲ ወኪሎች ውጪ ማንኛውም አካል የመራጮች ምዝገብ እና ተመዝጋቢዎች መረጃን አስመልክቶ ምርጫ ጣቢያም ሆነ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎችን እንዳይጠይቅ እንዲሁም በምርጫ ጣቢያው ውስጥ እና በ200 ሜትር ርቀት ዙሪያ እንዳይገኝ  

3. ማንኛውም የመንግስት እርከን ሰራተኛ ከቦርዱ የበላይ ሃላፊዎች እውቅና በማግኘት ወይም በልዩ የደህንነት ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ለምርጫ አስፈጻሚች ከምርጫ ጋር የተገናኘ ቁሳቁሶችን እንዲያቀንቀሳቅሱ፣ ትእዛዝ አቅጣጫ እና ጥቆማ እንዳይሰጥ እጅግ በጥብቅ ያሳስበባል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም እንደዚህ አይነት ጣልቃ ገብነቶች እና መሰል ክልከላዎች በተለይ ድምጽ መስጫ ቀኑ እየቀረበ ሲመጣ በተግባር ላይ ማዋል ግድ መሆን አለበት ይላል። 

ማጣቀሻዎች: 

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ሙሉ ማሳሰቢያ: 

https://www.facebook.com/National-Electoral-Board-of-Ethiopia-NEBE-የኢትዮጵያ-ብሔራዊ-ምርጫ-ቦርድ-414693405979601 

– የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቀጥር 1162/2019

https://nebe.org.et/sites/default/files/Ethiopian-Electoral-Proclamtion-No-1162.

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::