አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ ግለሰብ የፖለቲካ ፓርቲን ወክሎ በምርጫ ለመወዳደር ዕጩ መሆን ይችላል?

የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆነ ግለሰብ በሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ መሆን ይችላል?

ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ለመሆን በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ክልል 16 የብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው ተመዝግበዋል። ዶክተር ሲሳይ በብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪነት ይመዝገቡ እንጂ የፓርቲው አባል አለመሆናቸውን ይናገራሉ። ከቀናት በፊት በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ብልጽግናን ወክዬ በዕጩነት ተመዘገብኩ አልኩ እንጂ የብልጽግና አባል ሆኛለሁ ማለት አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባልነታቸው ይታወቁ የነበሩ የተወሰኑ ግለሰቦች በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ክልሎች የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በመሆን ተመዝግበዋል።

እነዚህን ሁለት ጉዳዮች በተመለከተ በርከት ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚ ዜጎች “አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ ግለሰብ የፖለቲካ ፓርቲን ወክሎ በምርጫ ለመወዳደር ዕጩ መሆን ይችላል?” እና “የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆነ ግለሰብ በሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ መሆን ይችላል?” የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ፣ የድጋፍ ፊርማ አሰባሰብ እና መለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 10 ቁጥር 2(ለ) መሰረት የፖለቲካ ድርጅት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ግንባር ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት እጩ ሆኖ የሚቀርብ ግለሰብ የፖለቲካ ድርጅቱ አባል መሆን አለበት።

በዚህ መመሪያ መሰረት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ የፓርቲው አባል መሆን አለባቸው፣ እንዲሁም በአብን አባልነት ይታወቁ የነበሩ ግለሰቦች የባልደራስ ዕጩ ተወዳዳሪ ለመሆን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አባል መሆን አለባቸው።

ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቃል አቀባይ ሶሊያና ሽመልስ አንድ ፓርቲን ወክሎ የሚቀርብ ዕጩ ተወዳዳሪ የፓርቲው አባል ተደረጎ እንደሚወሰድ አስረድተዋል።

ቃል አቀባዩዋ እንዳብራሩት “አንድ እጩ ሲመዘገብ ፓርቲው ይሄንን ግለሰብ በእጩነት እያቀረብኩ ነው ብሎ የሚሞላው ፎርም አለ፣ በዚህ መሰረት አንድ ፓርቲ አንድ ግለሰብን እጩ አድርጎ ካቀረበው አባሌ ነው ብሎ ተቀብሎት ነው ማለት ነው፣ የእጩ ምዝገባ የሚከናወነውም ፓርቲዎች ሲያቀርቡት ነው ስለዚህ assumption የሚሆነው ፓርቲዎች አባላቸው የሆነውን እጩ ነው የሚያቀርቡት የሚል ነው። በዚህ መሰረት እጩው የቀረበበት ፓርቲ አባል ነው ተብሎ ነው የሚቆጠረው፣ ትክክል አይደለም የእኔ አባል ሆኖ ለሌላ ተወዳደረ የሚል ፓርቲ ቅሬታና ተቃውሞ ማቅረብ ይችላል።”

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እንደሆኑ የሚታወቁት ዶክተር ቴዎድሮስ ኃማርያም በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ዕጩ ተወዳዳሪ በመሆን ተመዝግበዋል። ይህን ሲያደርጉ ከአብን አባልነትዎ ለቀዋል ወይ የሚል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ቼክ ቀርቦላቻው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በተያያዘ መረጃ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የአዲስ አበባ ምርጫ እድሉን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲጠቀምበት መፍቀዱን የባልደራስ ቃል አቀባይ ዶክተር በቃሉ አጥናፉ ዛሬ ለህትመት ለበቃው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ገልጸዋል። ዶክተር በቃሉ “የናንተን ድምጽ እንዳንከፋፈል ብሎ አብን አዲስ አበባን ለኛ ለቀቀልን” ሲሉ ለጋዜጣው ተናግረዋል። ሁለቱ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ጉዳይ በጋራ ለመንቀሳቀስ በቅርቡ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::