የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ይልቅ ወደ አስመራ ለሚደረግ ጉዞ የበለጠ ትኬት ዋጋ ያስከፍላል?

Does Ethiopian Airlines charge a higher ticket price for a trip to Asmara than Addis Ababa to Washington DC?

ነሐሴ 7፣ 2016 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንግስት በቅርቡ ይፋ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ለዉጥ መነሻ በማድረግ የትኬት ክፍያ ፖሊሲው ላይ ማሻሻያ አድርጓል።

ይህን መነሻ በማድረግም ወደ ሌሎች ሀገራት በሚደረጉ በረራዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ለውጥ ታይቷል፤ ስለ ጉዳዩም የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሀሳቦች ሲንሸራሸሩ ሰንብተዋል።

በማህበራዊ ትስስር ገጾች ከተጋሩ መረጃዎች አንዱ ደግሞ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወሺንግተን ዲሲ ይልቅ ወደ አስመራ የበለጠ ትኬት ዋጋ ያስከፍላል” የሚል ነው።

ይህን መረጃ ካጋሩት መካከል ደግሞ ‘Alg’ የሚል ስም ያለው የኤክስ (ትዊተር) አካውንት አንዱ ነው: https://x.com/girmatelk/status/1821643194154488036?s=46&t=dmcdufxK8i9nmLEWi2-yGQ

አካውንቱ “ከአዲስ አበባ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ በአየር 34 ሰዓታትን ይፈጃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትኬት ዋጋም 95 ሺህ ብር ነው። አንድ ሰዓት የሚፈጀው ከአዲስ አበባ- አስመራ ትኬት ዋጋ ደግሞ 108 ሺህ ብር ነው” ይላል።

ስለዚህም የኤርትራ መንግስት አየር መንገዱ የሀገሪቱን አየር ክልል እንዳይጠቀም መከልከል እንዳለበትም ጽፏል። ይህን መረጃም ከ40 በላይ የኤክስ ተጠቃሚዎች መልሰው አጋርተውታል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ መረጃ ዙሪያ ባደረገው ማጣራት መረጃው የተሳሳተ እንደሆነ አረጋገጧል። ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የሚደረግ ጉዞ ትኬት ዋጋም ከአዲስ አበባ- ዋሺንግተን ዲሲ የሚበልጥ አይደለም።

ይህን መረጃ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ-ገጽ እንዲሁም የሞባይል መተግበሪያ መመልከት የሚቻል ሲሆን ኢትዮጵያ ቼክ ለማሳያ ያክል ቀጣይ ሰኞ ነሐሴ 13፣ 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ሁለቱ ከተሞች የሚደረጉ የአንድ ሳምንት ቆይታ ያላቸው ደርሶ መልስ በረራዎች ትኬት ዋጋን ተመልክቷል።

በዚሁ መሰረት በእለቱ ሰኞ ነሐሴ 13፣ 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ በኢኮኖሚ ክፍል በረራ አድርጎ በሳምንቱ ነሐሴ 20፣ 2016 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የሚጠየቀው ዝቅተኛ የትኬት ዋጋ 233,477 ብር ነው።

በተመሳሳይ ቀናት ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እና ከአስመራ ወደ ከአዲስ አበባ ለሚደረግ ደርሶ መልስ በረራ የሚጠይቀው ዝቅተኛ ገንዘብ መጠን ደግሞ 101,599 ብር ነው።

ይህም ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ ለሚደረግ ጉዞ የሚከፈለው የትኬት ዋጋ ከአዲስ አበባ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ከሚደረግ ጉዞ ያነሰ መሆኑን ያሳያል።

የጉዞ ትኬት ዋጋ የበረራው መንገድ፣ ትኬት የተቆረጠበት ቀን እና ሌሎች ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ልዩነት የሚኖረው ቢሆንም ቀናትን በመቀያየር ባደረግነው የትኬት ዋጋ ምልከታ ወደ አስመራ ከሚደረጉ ይልቅ ወደ ወሺንግተን ዲሲ ለሚደረጉ ጉዞዎች የሚከፈለው የትኬት ዋጋ ብልጫ እንዳለው ተመልክተናል።

በዚህም መሠረት የተጋራው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ማየት ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::