የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ከሚረዱ እርምጃዎች መካከል መከተብ በቀዳሚነት ይጠቀሳል!

የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በቫይረሱ የመያዝ እድላችንን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ሲሆን ከተያዝንም በሽታው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስብን ይረዳል። የመከላከያ ክትባት ጠቀሜታው የጎላ ቢሆንም ክትባቱን በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ ይስተዋላል።

እነዚህ በሳይንስ ያልተደገፉ የተሳሳቱ መረጃዎች ዜጎች ክትባት ለመውሰድ እንዲያመነቱ የሚያደርጉ ሲሆን የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ለሚደረገው ጥረትም በተግዳሮትነት ይጠቀሳሉ።

ክትባቱን በተመለከ በስፋት ከሚሰራጩ የተሳሳቱና የተዛቡ መረጃዎች መካከል “ከዚህ በፊት በኮቪድ ቫይረስ ተይዤ ስለነበር/ስለዳንኩ ክትባቱን መውሰድ አይጠበቅብኝም” የሚለው ይገኝበታል።

በጤና ባለሙያዎች እይታ ግን እውነታው ይህ ነው: የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እና የመከላከያ ክትባቱን በተመለከተ እስካሁን የተደረጉ ጥናቶች በበሽታው ተይዘው ለሚያውቁም ሆነ ላልተያዙ ሰዎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መውሰድ በቫይረሱ ላለመያዝ የተሻለው አማራጭ መሆኑን ያሳያሉ። በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም ‘’ Reduced Risk of Reinfection with SARS-CoV-2 After COVID-19 Vaccination’’ በሚል ርዕስ የታተመ ሳይንሳዊ ጥናት እንዳሳየው በኮቪድ-19 ቫይረስ ተይዘው ካገገሙ በኃላ ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ካገገሙ በሗላ ክትባት ከወሰዱ ሰዎች አንጻር እንደገና በኮቪድ-19 ቫይረስ የመያዝ እድላቸው ከሁለት እጥፍ በላይ ይሆናል።

በተጨማሪም ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ምንም እኳን በበሽታው ተይዘው የነበሩ ሰዎች የተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ አቅማቸው በተወሰነ ደረጃ የሚገነባ ቢሆንም ከኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ጋር ሲወዳደር የመከላከል አቅሙ ውስን ነው። እንዲሁም ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች የገነቡት የመከላከል አቅም ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ በትክክል መናገር እንደማይቻል ጥናቶች ይጠቁማሉ።

የመረጃ ምንጭ: ጆን ሆፕኪንስ ሜዲስን

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::