በኮሮና ቫይረስ ክትባት ዙርያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች እና ሴራ ትንተናዎች!

ባሳለፍነው ቅዳሜ የኮሮና ቫይረስ ክትባት በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ግዜ መሰጠት ሲጀምር በርካታ የጤና ባለሙያዎች እና የስራ ሀላፊዎች ክትባቱን ወስደው ነበር። ሌሎች በርካቶች ደግሞ ክትባቱን ለመውሰድ ፈራ፣ ተባ ሲሉ እንደነበር ኢትዮጵያ ቼክ መረጃ አግኝቷል።

ለዚህ ሁሉ መነሻው ደግሞ በክትባቱ ዙርያ ሲሰራጩ የነበሩ ሀሰተኛ መረጃዎች እና በመረጃ ያልተደገፉ ሴራ ትንተናዎች ናቸው።

እንደ ሌሎች ክትባቶች ሁሉ የኮሮና ቫይረስ ክትባትም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል። ሆኖም በክትባቱ ዙሪያ የሚነገሩ እና በማህበረሰባችን ውስጥ እየተሰራጩ ያሉ የሀሰት መረጃዎች እና የሴራ ትንተናዎች በብዛት አሉ።

አንደኛው የአለም መንግስታት ይህን የኮሮና ቫይረስ ክትባት የአለምን ህዝብ ቁጥርን ለመቆጣጠር ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ የሚነገረው ነው። ሌላው እና በስፋት የሚሰራጨው የተሳሳተ መረጃ ደግሞ ታዋቂው ቢሊነር ቢል ጌትስ ይህንን ክትባት በመጠቀም የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሊጠቀምበት እንደፈለገ ነው።

በተጨማሪም ቫይረሱ መሀን ያረጋል፣ የ666 ፕሮጀክት ነው እንዲሁም የሰዎች ሰውነት ውስጥ ማይክሮ ቺፕ ለመቅበር የሚደረግ ጥድፊያ ነው የሚሉም አልታጡም።

እንዲህ አይነት ያልተረጋገጡ እና የሀሰት መረጃዎች ብዙ ያልተማረ ህዝብ ባለባቸው ሀገራት ላይ ጎላ ብሎ እንደሚታይ ጥናቶች ይጠቁማሉ። እንደ አሜሪካ ባሉ ያደጉ የሚባሉ ሀገራት ውስጥ ደግሞ በአንፃራዊነት በትምህርት ደረጃቸው ዝቅ ብለው የሚገኙ እንደ ጥቁሮች እና ላቲኖች ላይ በስፋት ይንፀባረቃል።

እንደ ጀርመን፣ ኖርዌይ እና እንግሊዝ ያሉ ሀገራት ደግሞ ሰሞኑን የአስትራዜንካ ክትባት በተወሰኑ ሰዎች ላይ የደም መርጋት አስከተለ መባሉን ተከትሎ ክትባቱን መስጠት አቁመው ነበር። ነገር ግን በትናንትናው እለት የአለም ጤና ድርጅት እና የአውሮፓ የጤና ማዕከል ችግሩ እንዳለ መረጃ እንደሌለ ማረጋገጫ ከሰጡ በሗላ ክትባቱን መስጠት ጀምረዋል።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ያናገራቸው የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በክትባቱ ዙርያ አሉ የተባሉ አንዳንድ ችግሮችን ከክትባቱ መድሀኒት ጋር ማያያዙ ትክክል እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

“እኛ እንደምናምነው የኮሮና ቫይረስ ክትባት የሚሰጠው ጥቅም አለ ተብሎ ከሚነገረው ጉዳት በእጅጉ የላቀ ነው፣ ለዚህም ነው ክትባቱን መስጠት ያላቆምነው” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግራዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ትናንት ድረስ ከ1,400 በላይ ሰዎች ክትባት እንደወሰዱ ተነግሯል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::