ዴልታ ስለተባለው የኮቪድ-19 ዝርያ አጭር መረጃ!

የኮቪድ-19 የዴልታ ዝርያ በኢትዮጵያ መገኘቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ የኮቪድ-19 የዴልታ ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት የሚችል፣ ሰዎችን ለከባድ ህመም የሚዳርግ እንዲሁም ለሞት የሚያበቃ አደገኛ ዝርያ እንደሆነም ገልፀዋል።  

ለመሆኑ ዴልታ ከሌሎች የኮቪድ ዝርያዎች በምን ይለያል? 

1. ከሌሎች የኮቪድ ዝርያዎች አንጻር ዴልታ የመዛመት ፍጥነቱ ከፍተኛ ነው። የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) እንደሚለው ይህ ዝርያ ቀደም ካሉት የኮቪድ-19 ዝርያዎች አንጻር የመዛመት ፍጥነቱ ከሁለት እጥፍ በላይ ነው። ዝርያው በጥቅምት ወር በህንድ አገር ብቅ ያለ ሲሆን በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት በነሀሴ ወር መጀመሪያ ከ142 በላይ ሀገሮችን አዳርሷል። በዚህም የተነሳ የዓለም ጤና ድርጅት በግንቦት ወር ዴልታን አሳሳቢ (Variants of Concern) ካላቸው የኮቪድ-19 ዝርያዎች ውስጥ መድቦታል። የዓለም ጤና ድርጅት ከዴልታ በፊት አልፋ፣ ቤታና ጋማ የተሰኙ ዝርያዎችን በአሳሳቢነት መመደቡ ይታወቃል። 

2.ዴልታ ለከባድ ህመም የሚዳርግ፣ ለሞት የሚያበቃ አደገኛ ዝርያ ነው። በካናዳና በስኮትላንድ የተደረጉ ሁለት የተለያዩ ጥናቶች እንዳሳዩት በዴልታ ዝርያ የተያዙ ሰዎች ለከባድ ህመም የመዳረግ እድላቸው ከፍተኛ ሲሆን ብዙዎችም በሆስፒታል ተኝተው ለመታከም ይገደዳሉ። በተለይም የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ባልወሰዱ ሰዎች ላይ የህመሙ ብርታትና የሞት ምጣኔው ከፍ ያለ ነው። 

3.የዴልታ ዝርያ በተለይም ባልተከተቡ ሰዎች ላይ ይበረታል። ይህ ዝርያ በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን የሚያጠቃ ሲሆን ያልተከተቡ ሰዎች የመያዝ እንዲሁም ከበድ ላለ ህመምና ሞት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ዶክተር ሊያም ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኮቪድ-19 ክትባትን ሕብረተሰቡ በየጤና ተቋማቱ በመገኘት እንዲወስድ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በበኩሉ የዴልታ ዝርያ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ሕብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር ከዚህ በፊት ያደርገው ከነበረው በበለጠና በተጠናከረ ሁኔታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክን ሁልጊዜና በአግባቡ ማድረግ፣ የእጅ ንፅህናን መጠበቅ ወይም ሳኒታይዘር መጠቀም እንዲሁም አላስፈላጊ መሰባሰቦችን መቀነስ እንዳለበት አሳስቧል። 

በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመያዝ ምጣኔውም ከ1 በመቶ ወደ 20 በመቶ ያሻቀበ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ብቻ 8,300 ሰዎች  በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲያዙ 118 ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::