“አርበኛ በላይ ዘለቀ ቂልጡ ማነው?” በሚል በኢቢሲ እንደተሰራ ተደርጎ የቀረበ የቅንብር ምስል! 

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) በትናንትናው እለት እንደተፃፈ ተደርጎ እና ተቀናብሮ የቀረበ አንድ ምስል የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ምስሉ “አርበኛ በላይ ዘለቀ ቂልጡ ማነው?” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን በቀጣይ ሶስት መስመሮች ደግሞ የአርበኛውን ወላጅ ቤተሰቦች እና የትውልድ ስፍራ ይጠቅሳል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ቅኝት/ዳሰሳ ይህ ዜና በሚድያ ተቋሙ ላይ ቀርቦ እንዳልነበር እና በቅንብር ተሰርቶ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተለቀቀ እንደሆነ ማረጋገጥ ችሏል፣ ይህንን ከኢቢሲ ሳይበር ሚድያ ክፍልም አረጋግጧል። ብዙዎች ግን ፅሁፉ በኢቢሲ ከቀረበ በኋላ ትንሽ ቆይቶ እንደጠፋ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፣ ይህ ግን ትክክል እንዳልሆነ ጠቋሚ ምልክቶች አሉ። 

ሀሰተኝነቱን የሚያረጋግጡ ምን ምልክቶች አሉ? 

– ኢቢሲ ማህበራዊ ሚድያዎች ላይ የሚጠቀምበትን ምልክት (logo) የተመለከትን ሲሆን በቅንብር የቀረበው ምስል ላይ ጎላ ብሎ ተሰርቶ ቀርቧል (በቀስቱ ተጠቁሟል)። 

– በሌላ በኩል “አርበኛ በላይ ዘለቀ ቂልጡ ማነው?” የሚለው ከአርበኛ በላይ ዘለቀ ምስል ስር የተቀመጠው ፅሁፍ የተፃፈበት የፊደል አይነት (font) ኢቢሲ ከሚጠቀምበት “NOKIA” ከሚባለው ፊደል የተለየ እንደሆነ ለማየት ችለናል (ይህም በቀስት ተጠቁሟል)። 

– በመጨረሻም፣ ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተዘዋወሩ ያሉት ሁሉም የስክሪን ቅጂዎች (screenshots) ዜናው ከተለጠፈ 19 ደቂቃ እንደሆነው ይጠቁማሉ። ከዛ ውጪ በሌላ ሰው በሌላ ደቂቃ ላይ የተወሰደ የስሪን ቅጂ አለመኖሩ ምስሉ በቅንብር እንደተሰራ ሌላው ጠቋሚ ነጥብ ነው (በቀስት ተጠቁሟል)።  

ሆን ተብለው እና ተቀናብረው የሚለቀቁ ፅሁፎችን፣ ምስሎችን እንዲሁም ቪድዮዎችን ሳናረጋግጥ ባለማጋራት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እንከላከል። 

*** በዚህ መረጃችን ላይ ያጣራነው ዜናው በኢቢሲ ላይ አለመቅረቡን እንጂ ስለ አርበኛ በላይ ዘለቀ የቀረበው መረጃ ትክክለኛነትን ወይም ሀሰተኝነትን እንዳልሆነ ለመግለፅ እንወዳለን። ወደፊት በዚህም ዙርያ ማጣራት አድርገን ለመመለስ እንጥራለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::