ዩትዩብ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ክትባቶች ዙርያ ያወጣውን አዲስ መመሪያ የሚጥሱ ቻናሎች ላይ እስከመዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ይፋ አድርጓል!

ዩትዩብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝንና መከላከያ መንገዶችን በተመለከተ የሚሰራጩ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ለመቆጣጠር ከዓመት በፊት ተግባር ላይ ባዋለው መመሪያ ላይ ተጨማሪ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።

በማሻሻያው መሰረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች የተጨመሩ ሲሆን ድንጋጌዎችን በመጣስ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በሚያሰራጩ ቻናሎች ላይ እስከመዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ተጠቅሷል።

አዲሱ የዩትዩብ መመሪያ በዓለም የጤና ድርጅትና በሚመለከታቸው የጤና ተቋማት እውቅና የተሰጣቸውን የኮቪድ-19 ክትባቶችን በተመለከተ የመከላከል አቅማቸውን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ይዘትን ማጋራትን ይከለክላል። እንዲሁም ክትባቶችን በተመለከተ ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸውን የጎንዮሽ ጉዳቶች በዩትዩብ ቻናሎች ማሰራጨትን ይከልክላል። በተጨማሪም የኮቪድ-19 ክትባቶች የተሰሩበትን የንጥረ ነገር ይዘት የተመለከቱ የተዛቡ መረጃዎችን ማጋራትን ይከለክላል።

ድርጅቱ በአዲሱ መመሪያው የተከለከሉ ብሎ በምሳሌነት ከዘረዘራቸው መካከል የኮቪድ-19 ክትባቶች እንደ ካንሰር፣ የስኳር በሽታና ሌሎች ዘላቂ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ያስከትላሉ የሚሉ ይዘቶች፤ የኮቪድ-19 ክትባቶች ክትባቱን የወሰዱ ሰዎችን ለመከታተልና ለመለየት የሚረዱ ቁሶችን የያዙ ናቸው የሚሉ ይዘቶች፤ ክትባቶቹ የሰዎችን የጀነቲክ መዋቅር ይቀይራሉ የሚሉ ይዘቶች፤ ክትባቶቹ የስነ-ህዝብ ምጣኔን ይቀንሳሉ የሚሉ ይዘቶች እንዲሁም ሌሎች የሴራ ትንተናን የተመለከቱ ይገኙበታል።

ይሁን እንጂ የኮቪድ-19 ክትባቶችን በተመለከተ አላማቸው ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት ያልሆኑ ትምህርታዊ፣ ኪነጥበባዊና ሳይንሳዊ ይዘቶችን ማጋራት እንደሚቻል ዩትዩብ በአዲሱ መመሪያው አስታውቋል። በተጨማሪም ግለሰቦች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን ከወሰዱ በኃላ የተሰማቸውን ስሜት ማጋራት እንደሚችሉም ገልጿል።

መመሪያውን በመጣስ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በሚያሰራጩ የዩትዩብ ቻናሎች ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ እስከመዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ተጠቅሷል። ዩትዩብ ከዓመት በፊት የኮቪድ-19 ወረርሽኝንና መከላከያ መንገዶችን በተመለከተ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ለመቆጣጠር መመሪያ ካወጣበት ጊዜ ጀምሮ ጥሰት የፈጸሙ 130,000 ይዘቶችን አስወግዷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::