ከሰሞኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከትግራይ ወደ አማራ ክልል የገቡበት ምክንያት ምን ነበር?

ከሰሞኑ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ዜጎች ከትግራይ ወደ አማራ ክልል እንደገቡ የሚጠቁሙ በርካታ ዜናዎች በተለይ በመንግስት እና በህዝብ ሚድያዎች ተዘግበዋል። በቅርብ ቀናት ወደ ቆቦ ብቻ የተሰደዱት የእነዚህ ዜጎች ቁጥር ከ60 ሺህ ማለፉን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

እነዚህ ዜናዎች በዘገባቸው ዜጎቹ በተለይ ወደ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች ያቀኑት “በክልላቸው የሚደርስባቸው ግፍ እና በደል ስለከበዳቸው ነው” የሚል ተመሳሳይ ዜና በኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት፣ በፋና ብሮድካስቲንግ ወዘተ ተዘግቧል።

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት በትናንትናው እለት ይፋ ባደረገው የግጭት ማቆም ውሳኔ ላይ “በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሰብዓዊ እርዳታን ፍለጋ ወደ አጎራባች ክልሎች እየተጓዙ መሆኑ እየተስተዋለ ነው” በማለት አስረድቷል።

ውሳኔው አክሎም “በትግራይ አጎራባች ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች ከትግራይ ክልል የሚመጡ የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ዜጎችን ተቀብሎ በማስተናገድ እያሳዩ ያለው በጎ ተግባር በህዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት እና የአንድነት መንፈስ የሚያሳይ ነው። መንግስት እነዚህ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታው ከቀያቸው ሳይፈናቀሉ ባሉበት እንዲርሳቸው ቢደረግ እንግልታቸውን እንድሚቀንስ በጽኑ ያምናል። በመሆኑም መንግስት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎቹን ችግር በአፋጣኝ የመፍታት ኃላፊነቱ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን በመረዳት የአስቸኳይ የሰብዓዊ አቅርቦቶች ወደ ትግራይ ክልል በበቂ ሁኔታ መድረስ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማሳካት የተቻለውን ሁሉ ጥረቶች ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል” ይላል።

ኢትዮጵያ ቼክ ከብሄራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ያገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ዜጎች ማንኛውንም ድጋፍ እናገኛለን ወዳሉበት ቦታ ሁሉ በእግራቸው ጉዞ ማድረግ ጀምረዋል።

ስለዚህ በነዚህ ሚድያዎች እንደተዘገበው ብቻ ሳይሆን የዜጎቹ እንቅስቃሴ ከምግብ እጦት ጋርም የተያያዘ መሆኑን ማየት ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::