ትዊተር ከሰሞኑ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ከሮይተርስ እና ኤፒ ጋር ያደረገው ጥምረት ምንድን ነው?

ትዊተር ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት ለመግታት ያለመ ጥምረት ከአሶሼትድ ፕሬስ (ኤፒ) እና ከሮይተርስ የዜና ወኬሎች ጋር መፍጠሩን ባሳለፍነው ሰኞ በድረገጹ ባስነበበው አጭር መጣጥፍ ይፋ አድርጓል። 

በመጣጥፉ እንደተገለጸው በትዊተር መድረክ (platform) ለሚወጡ ትኩስ መረጃዎች ከዜና ወኪሎች ጋር በመተባበር አውድ (context) የሚያሳዩ ማብራሪያዎችን  ለተጠቃሚዎች ያቀርባል። ለምሳሌ  ትሬንድ(Trends) በመባል በሚታወቀው የትዊተር ንዑስ መገልገያ ከአሶሼትድ ፕሬስ ወይንም  ከሮይተርስ የዜና ወኪሎች የተወሰዱ አውድ ሰጭ አጭር ማብራሪያዎች እንዲሁም ማስፈንጠሪያዎች (links) የሚካተቱ  ይሆናል። 

በተመሳሳይ በከፍተኛ ሁኔታ የመሰራጨት አዝማሚያ የሚታይባቸውን መረጃዎች ወይንም  ርዕሶች ከላይ ከተጠቀሱት የዜና ወኪሎች ጋር በመቀናጀት አውድ  የሚያሳዩ ማብራሪያዎችን በመጨመር ንቁ ምላሽ ለመስጠት  መዘጋጀቱን ትዊተር በመጣጥፉ አትቷል። 

በተጨማሪም ጥምረቱ ትዊተር  ባሳለፍነው ጥር ወር ለጀመረው በርድዋች (Birdwatch) የተሰኘ አገልግሎቱን ለማጠናከር እንደሚያግዘው ገልጿል። በርድዋች  የትዊተር ተጠቃሚዎች መረጃ እንዲያነጥሩ ለማስቻል የተጀመረ አገልግሎት መሆኑ ይታወቃል። 

ይህ ትዊተር ከኤፒ እና ሮይተርስ ጋር በመጣመር የጀመረው አገልግሎት ለጊዜው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለሚወጡ ትዊቶች ብቻ ያገለግላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::