ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተዘዋወረ የሚገኘው ኮ/ር ደራርቱ ቱሉን የሚያሳየው ቪድዮ ምንድን ነው? 

ዛሬ ከንጋት ጀምሮ በርካታ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች፣ ዲጂታል ሚድያዎች እንዲሁም ቻናሎች እና ገፆች አንድ ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ ድምጿን ከፍ አርጋ እያወራች የሚታይበትን ቪድዮ እያሰራጩ ይገኛሉ። 

ይህን ቪድዮ በተመለከተ በርካታ መላምቶች እየቀረቡ ሲሆን በርካታ ተከታታዮቻችንም እንድናጣራ ጠይቀውናል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ከደቂቃዎች በፊት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኮ/ር ደራርቱ ቱሉን አነጋግሯል። ኮ/ር ደራርቱ ቪድዮው ከቶክዮ ኦሎምፒክ በፊት ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በነበረ አለመግባባት ወቅት እንደነበር አስረድታለች። 

“የቆየ ቪድዮ ነው፣ ያኔ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፌዴሬሽኑን አግልሎ ስብሰባ ባረገበት ወቅት የተነሳ ነው” ብላ ምላሽ ሰጥታለች። 

ቪድዮው የአምና መሆኑን የፌዴሬሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ስለሺ ብስራትም ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጠዋል። 

አምና መጋቢት ወር ላይ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ጋር በተያያዘ ውዝግብ መከሰቱ ተዘግቦ ነበር። በወቅቱ በኮሚቴው ጽህፈት ቤት ውስጥ ተካሄደ የተባለን ስብሰባ ተከትሎ በአካባቢው ተቃውሞ እንደነበርም ይታወሳል። 

የተቃውሞ ሠልፉን ያደረጉት ሲያስረዱም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እያደረገ ይገኛል ያሉትን ሕገ ወጥና አግባብ ያልሆነ አሰራርን በመቃወም ነው ብለው ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::