የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ከኢትዮጵያ ለቆ ሊወጣ ስለመዘጋጀቱ የሚገልጹ መልዕክቶች ባለፉት ጥቂት ቀናት በስፋት ሲዘዋወሩ ተመልክተናል!

መልዕክቶቹን ያጋሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ድርጅቱ ኢትዮጵያን ለመልቀቅ መዘጋጀቱን ይጥቀሱ እንጂ ምንጭ ሲጠቅሱ አልታዩም።

አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ በኦፊሴላዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ እያካሄዳቸው ያሉ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር መርሐግብሮቹ እንደሚቀጥሉ አስታውቋል።

ኤምባሲው ‘’በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚደረጉ ህይወት አድን የሰብዐዊ እርዳታዎች፣ የኮቪድ ምላሽና የኮቪድ መከላከያ ክትባት ድጋፍ፣ በጤናና በትምህርት ላይ ፈሰስ የሚደረጉ ድጋፎች እንዲሁም የድህረ ግጭት ማገገሚያ እቅዶች’’ መቀጠላቸውን ገልጿል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ክፍት መሆኑንም አስታውቋል።

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎቹ ሀገሪቱን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱና አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል በመወትወት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::