ለተማሪዎች ሰርቪስ በሚሰጡ ታክሲዎች ዙርያ “ሀሰተኛ” የሆነው መረጃ የቱ ነው? 

ለተማሪዎች ሰርቪስ የሚሰጡ ታክሲዎች ፈቃድ ባወጡበት የትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ እንዲሰጡ ማሳሰቡ ይታወሳል። ከዚህ ውጭ የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች “ህገ-ወጥ” ናቸው ሲሉ የቢሮው የኮሚውኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ይመሩ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸውም ነበር። 

ከቀናት በኋላ ቢሮው ”አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል በሚል የሚሰራጨው መረጃዎች ሀሰተኛ ናቸው” አስታውቋል። ለመሆኑ ሀሰተኛ የሆነው መረጃ የቱ ነው? 

ከዚሁ መረጃ ጋር ተያይዞ በድጋሜ በስልክ ያገኘናቸው አቶ አረጋዊ ሀሰተኛ የተባለው ”ሙሉ ለሙሉ ታክሲዎች ይህንን አገልግሎት አቁሙ መባሉ ነው። ፈቃድ ያላቸው ይህንን የሰርቪስ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ” ብለዋል። 

በተጨማሪም ”ይህንን አስመልክቶ የተዘጋጀ አዲስ መመሪያ የለም ከዚህ ቀደምም ማሳሰቢያ ነው የሰጠነው እስካሁን ወደ ቅጣትም ወደ ትግበራም አልገባም” ብለዋል።”  

አቶ አረጋዊ ከቀናት በፊት ለዚህ ጉዳይ ፈቃድ የተሰጣቸው ባለታክሲዎች ስለመኖራቸው ጠይቀናቸው ”ለየትኛውም የታክሲ ፈቃድ ላለው አካል የሰርቪስ ሥራ እንዲሰራ ፈቃድ አልተሰጠውም” ሲሉ መልሰው ነበር። 

ከዚህ ቀደም የተወሰኑ ታክሲዎች ብቻ በዚህ ሥራ መሰማራታቸው ጉዳዩ የታለፈ እንደሆነና ዘንድሮ ግን ቁጥሩ የተጋነነ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ሰርቪስ መሆናቸው አፋጣኝ እርምጃ እንድንወስድ አስገድዶናል ሲሉ ገልጸው ነበር። 

ሆኖም ከታክሲ ማህበራትና ከዚህ ቀደም ከነበረው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ፈቃድ ያገኙ እንዳሉ በቁጥራቸው ግን ጥቂት መሆናቸውን ገልጸዋል። አሁን የተፈጠረው ችግር ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ታክሲዎች በዚህ አገልግሎት መሳተፋቸው ነው ብለዋል። 

የጠራው መረጃ ምንድን ነው? 

– የተማሪዎች ሰርቪስን በተመለከተ አዲስ መመሪያ እስኪወጣ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን ሲሰጡ የነበሩ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ታክሲዎች በነበሩበት ሥራ እንዲቀጥሉ፣ 

– ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ታክሲዎች በተማሪዎች የሰርቪስ አገልግሎት ላይ በመሰማራታቸው በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ስለሚገኝ በተመደቡበት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰማሩ የሚል ነው። 

ስህተቱ ምን ነበር? 

– መረጃው በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ሲንሸራሸር አዲስ መመሪያ እንደጸደቀ፣ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱ እንዲቆም በሚል ተዛብቶ መሰራጨቱ፣ 

– መረጃው ሲወጣ የሚፈጥረውን ችግር በሚገባ አጥንቶ የወጣ ባለመሆኑና ዝርዝር መረጃ ተያይዞ ባለመውጣቱ ለብዥታው ምክንያት ሆኗል። 

ጥንቃቄ! 

– በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚንሸራሸሩ መረጃዎች የመበረዝ እድላቸው ሰፊ ነው። በመሆኑም መረጃዎችን በተቻለ አቅም ከምንጩ ወይም ከታማኝ ምንጮች ጠንቅቆ መረዳት ያሻል። 

– ተቋማት የህዝብን ድምፅ ሰምተው አቋማቸውን መፈተሽና ማስተካከል ይችላሉ፤ የተገባም ነው። ሆኖም ከተቋሙ የወጣን መረጃን ሙሉ ለሙሉ ሀሰተኛ ማለት ተገቢ አይደለም። መረጃው ተበርዞ ከሆነም ሙሉ ለሙሉ ሀሰተኛ ብሎ መፈረጅ ሳይሆን የተቀየጠ ብሎ በደረጃው ማስቀመጥ ያሻል። 

Via Tikvah Magazine

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::