ታይም መጽሔት ተጽዕኖ ፈጣሪ ያላቸውን ግለሰቦች ለመምረጥ ምን መስፈርት ይጠቀማል? 

ታዋቂው የእንግሊዘኛ ቋንቋ መጽሔት ታይም ትናንት የ2022 ተጽዕኖ ፈጣሪ ያላቸውን መቶ ግለሰቦች ይፋ አድርጓል። በተጽዕኖ ፈጣሪነት ከተካተቱት መካከል ጠቅላይ  ሚኒስትር አብይ አህመድና አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ትምኒት ገብሩ ይገኙበታል። 

ታይም መጽሔት ተጽዕኖ ፈጣሪ ያላቸውን ግለሰቦች ለመምረጥ ምን መስፈርት ይጠቀማል? 

ታይም በየዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው ያላቸውን መቶ ግለሰቦች ይፋ ከማድረጉ ከሰዐታት በፊት የምርጫውን መስፈርትና የመራጮችን ማንነት የሚያስረዳ ማስታወሻ በመጽሔቱ ዋና አርታዒ በኩል ያስነብባል። 

ይህን ልማድ ተከትሎም የ2022 መቶ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ይፋ ከመደረጋቸው በፊት የመጽሔቱ ዋና አርታዒ ኤድዋርድ ፊልስነታል “How We Chose the 2022 TIME100” በሚል ርዕስ ምርጫውን የተመለከተ ማስታወሻ አስነብቧል። 

ኤድዋርድ ፊልስነታል የ2022 ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ለመምረጥ አንድ ብቸኛ መስፈርት ጥቅም ላይ መዋሉን የገልጸ ሲሆን እሱም “ተጽዕኖ መፍጠር” (influence) መሆኑን አብራርቷል። ተጽዕኖ መፍጠር ሁለት ገጽታ አለው በማለት በማስታወሻው ላይ ያሰፈረው ዋና አርታዒው “በጎ” እና “መጥፎ” ተጽዕኖ መሆናቸውን አጽኖት ሰጥቶበታል። 

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዜሊንስኪና የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን በ2022ቱ ምርጫ መካተታቸው የተጽኖ ፈጣሪነትን ሁለት ገጽታዎች እንደሚያሳዩም በምሳሌነት ጠቅሷል። 

ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን የሚመርጡት እነማን ናቸው? 

ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን የሚመርጡት በታይም መጽሔት የሚሰሩ በየደረጃው ያሉ አርታዒያን ሲሆን በዜና ክፍል የሚሰሩ ጋዜጠኞች ተጨማሪ ግብዐት በማቅረብ ይሳተፋሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::