– “ወደ ሀገር ቤት የገቡ ዲያስፖራዎችን ቁጥር ኢሚግሬሽን እንዲያሳውቀን በደብዳቤ ጠይቀናል፣ ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው”— የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ ቼክ

– “መቶ ሺህ ገደማ የሚሆኑ ዲያስፖራዎች ጥሪውን አክብረው ወደ ሀገር ቤት መጥተዋል”— ጋዜጣ ካፒታል ምንጩን ጠቅሶ ትናንት የዘገበው

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የሚጋብዝ ጥሪ በትዊተር ገጻቸው አጋርተው ነበር።

የፈረንጆችን የገና በዓልና አዲስ ዓመት እንዲሁም የኢትዮጵያን ገና አስታኮ የተላለፈው መልዕክት እስከ ታህሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ወደ ሀገር ቤት ለማምጣት ያለመ ነበር። ከመልዕክቱ ጋርም ‘#GreatEthiopianHomeComing’ የሚል ሃሽታግ ተያይዟል።

ጥሪውን ተከትሎም በርከት ያሉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መጓዛቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች በመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፉ የነበረ ሲሆን እነሱን ማዕከል ያደረጉ የጉብኝትና የውይይት መርሐግብሮች ሲደረጉም ተመልክተናል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የአንድ ሚሊዮን ጥሪ ከቁጥር አንጻር ስለመሳካቱ በርከት ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጥያቄ ሲያነሱ አስተውለናል። አንዳንዶች ደግሞ በውጭ ሀገር የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት ቁጥርን በተመለከተ ጥርጣሪያቸውን ሲገልጹ ተመልክተናል።

ኢትዮጵያ ቼክ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የመጡ የዲያስፖራና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ትክክለኛ ቁጥር ለማጣራት መርሐግብሩን በዋናነት ሲያስተናበር የነበረውን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲን አነጋግሯል።

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንድወሰን ግርማ “ትክክለኛው ቁጥር ለጊዜው በእጃችን የለም፣ ይህን ሊያውቀው የሚችለው የኢሚግሬሽን ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ነው። ወደ ሀገር ቤት የገቡ ዲያስፖራዎችን ቁጥር እንዲያሳውቁን በደብዳቤ ጠይቀናል፣ ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው” የሚል መልስ ሰጥተውናል።

ሳምንታዊው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ካፒታል አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንን ጠቅሶ ወደ “መቶ ሺህ ገደማ” የሚሆኑ ዲያስፖራዎች ጥሪውን አክብረው ወደ ሀገር ቤት መምጣታቸውን በትናት ዕትሙ አስነብቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት እስከ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተሰራጭተው እንደሚኖሩ የሚገልጹ መረጃዎችን በተለያዩ ወቅቶች መግልጹ የሚታወቅ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ-ህዝብ ክፍል በበኩሉ ቁጥሩ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑን ይገልጻል። የተመድ የስነ-ህዝብ ክፍል እ.አ.አ በ2020 ዓ.ም ያወጣው መረጃ በውጭ የሚኖሩና ትውልዳቸው ከኢትዮጵያውያ የሆኑ ሰዎች ቁጥር 946 ሺህ መሆኑን ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሪውን ባቀረቡበት ወቅት አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ዜጎቻቸውን ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ይጎተጉቱ እንደነበር ይታወሳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::