የተ.መ.ድ. የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት እና በተለየ መልኩ ተተርጉሞ የቀረበው ዜና!

በሱዳን መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኙ የነበሩ ከትግራይ ክልል የመጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ሰሞኑን አንድ ሪፖርት አውጥቶ ነበር።

ይህ ጳጉሜ 2 የወጣ ሪፖርት እንደሚጠቅሰው ኮሚሽኑ ጉዳዩን በተመለከተ የወጡ የሚድያ ሪፖርቶች መኖራቸውን እንደሚያውቅ ነገር ግን “ወደመጡበት ሃገር የተመለሱትን ጨምሮ ከስደተኞች ካምፕ ወጥተው የሄዱት ስደተኞች ያሉበትን ቦታ ማረጋገጥ አልቻልንም” በማለት ይገልጻል። በዚሁ የመንግስታቱ ድርጅት መግለጫ ከቅርብ ወራት ወዲህ በስደተኛ ካምፖቹ ውስጥ መጠነኛ የሚባል የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር መቀነስ የታየ ስለመሆኑም ይጠቅሳል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ደግሞ ዛሬ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ ላይ እነዚህ ስደተኞች “ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በጦርነት መሳተፋቸውን [ኮሚሽኑ] ባወጣው መግለጫ አመለከተ” ብሏል።

ይህ ዜና በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት የፌስቡክ ገጽ ላይ የቀረበ ሲሆን፣ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ድርጅቱ የተፈጠረውን የትርጉም ስህተት አርሞ እና አስተካክሎ ወጥቷል። የእርምት ዜናውም “የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ከትግራይ ክልል ወጥተው በሱዳን መጠለያ ጣቢያ የነበሩ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በጦርነት ይሳተፉ ወይም የት ይሂዱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገለጸ” ይላል፣ የፋና ዜና ግን ሳይቀየር አሁንም ይታያል።

የበለጠ ለመረዳት ይረዳ ዘንድ የተጠቀሱትን ሁለቱንም ይዘቶች ቀጥሎ ያሉትን አገናኞች ይከተሉ:
https://www.facebook.com/123960474361367/posts/4371814166242622/?d=n
https://www.unhcr.org/news/press/2021/9/613736584/unhcr-statement-on-ethiopian-refugees-registered-in-sudan-allegedly-involved.http

በሱዳን ተጠልለው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ በጦርነቱ እየተሳተፉ እንደሚገኙ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ቆይቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::