ትዊተር የግለሰቦችን ፎቶና ቪዲዮ ካለፈቃድ ማጋራት የሚከለክል ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል!

ትዊተር ይህን የገለጸው ግለሰባዊ መረጃዎችን የሚመለከተውን ፖሊሲ ጠበቅ ማድረጉን ባስነበበት ረዘም ያለ ብሎግ ሲሆን ማሻሻያውን ያደረገው በተለይም በአክቲቪስቶች፣ በሴቶች፣ በተቃዋሚዎች እንዲሁም አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ማህበረሰቦች ላይ የሚቃጡ ማሸማቀቆችንና ትንኮሳዎችን ለመቆጣጠር መሆኑን ገልጿል።

በአዲሱ መመሪያ መሰረትም ፎቶው ወይንም ቪዲዮው ካለፈቃዱ የተጋራበት ግለሰብ ወይንም ህጋዊ ተወካዩ ለትዊተር ሪፖርት ማደረግ የሚችል ይሆናል። ትዊተርም ሪፖርቱን ከመረመረ በኋላ ፎቶውን ወይንም ቪዲዮውን ማስወገድን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎችን ይወስዳል።

ሆኖም ፎቶው ወይንም ቪዲዮው የታዋቂ ግለሰብ አልያም ከህዝብ ፍላጎት አኳያ ሚዛን የሚደፋ ከሆነ አዲሱ ፖሊሲ ተፈጻሚነት አይኖረወም። ሆኖም ድርጊቱ ግለሰቡን ለማሸማቀቅ፣ ለማስፈራራት ወይንም ዝም ለማሰኘት መዋል የለበትም ይላል። በተጨማሪም ግለሰቦችን ለመርዳት ታስበው የሚጋሩ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን አዲሱ ፖሊሲ እንደሚታገስ ትዊተር ገልጿል።

ትዊተር ከዚህ ቀደም የግለሰቦችን አድራሻ ወይንም መገኛ ቦታ፣ የመታወቂያ ካርድ፣ የግል ስልክ ቁጥሮችንና ኢሜሎችን፣ የባንክ አካውንት ቁጥሮችን፣ የህክምና መረጃዎችን እና ሌሎችን የግል መረጃዎች ማጋራት የሚከለክል ፖሊሲ እንዳለው ይታወቃል። በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎችን ይፋ አደርጋለሁ ብሎ ማስፈራራትንም ይከለክላል።

በተያያዘ መረጃ ትዊተር ለኢትዮጵያ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቁ አካውንቶችና ሃሽታጎች ላይ ያልተገባ እርምጃና አፈና ይወስዳል ተብሎ ለሚቀርብበት ክስ ምላሽ ሰጥቷል። የትዊተር ቃል አቀባይ ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የእንግሊዘኛ ክፍል እንደተናገሩት ትዊተር እርምጃ የሚወስደው ተጨባጭ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። ድረጅታቸው ከፖለቲካ “ገለልተኛ” መሆኑንም አስታውቀዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::