ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ‘ሸኔ’ እስካሁን ባለው ሂደት በህግ በአሸባሪነት ተመድበዋል?

ባሳለፍነው ቅዳሜ (ሚያዝያ 23/2013) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ‘ሸኔ’ በሽብርተኛነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል።

ይህን ተከትሎ አንዳንድ ሚድያዎች እና የማህበራዊ ሚድያ ፀሀፊዎች ድርጅቶቹ በህግ በአሸባሪነት መመደባቸውን ገልፀው ፅፈዋል፣ ይህም የህግ ሂደቱን በትክክል ካለመረዳት የመጣ ሊሆን እንደሚችል መረዳት ይቻላል።

ሂደቱ ምን ይመስላል?

በአዲሱ የፀረ-ሽብር ህግ መሰረት ጠቅላይ አቃቤ ህግ አንድ ድርጅት የሽብር ወንጀል መፈፀሙን ወይም እየፈፀ ስለመሆኑ ሲያምን ድርጅቱ በአሸባሪነት እንዲሰየም የውሳኔ ሀሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባል።

ከዚያም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ እንደወሰነው በጠቅላይ አቃቤ ህግ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ሲያፀድቀው ለተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ያቀርባል።

ከዛም ምክር ቤቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመመርመር ውሳኔ ይሰጣል። በአዋጁ መሰረት በሽብርተኝነት የተሰየመ ድርጅት ስያሜው ተፈፃሚ ከሚሆንበት ግዜ ጀምሮ የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች ህጋዊ ውጤት አይኖራቸውም።

በአዋጁ መሰረት የሽብር ድርጊት መፈፀም ምን ማለት ነው?

– በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ
– የሰውን ህይወት ለአደጋ ያጋለጠ
– ሰውን ያገተ ወይም የጠለፈ
– በንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብት ወይም አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንዲሁም
– የህዝብ ወይም ማህበራዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ በከፍተኛ ሁኔታ ያስተጓጎለ እንደሆነ ነው።

ይህንን ድርጊት የፈፀመ ከ10 አመት እስከ 18 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል። ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱትን ለማስፈፀም የተፈፀመ ተግባር (ሰውን መግደል ወይም በታሪካዊ ወይም የባህል ቅርስ ወይም የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ) ከሆነ ከ15 አመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ነገ የሚያካሂድ ሲሆን ህወሓት እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::