ኢትዮጵያ ቼክ ባሳለፍነው በ2013 ዓ.ም ካጣራናቸው መረጃዎች መካከል ዓመቱን ያሳያሉ ብለን የመረጥናቸው አስር የተጣሩ መረጃዎች!

ባሳለፍነው በ2013 ዓ.ም በርካታ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ እና በመደበኛው ሚዲያ የተሰራጩበት ነበር። ኢትዮጵያ ቼክ ይህን የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት ለመዋጋት የበኩሉን ጥረት ኣአድርጓል። በመቶዎች የሚቆጠሩ መረጃዎችን ያጣራ ሲሆን ዓመቱን ያሳያሉ ያላችው አስር የተጣሩ መረጃዎችን መርጧል።

1. በመስቀል አደባባይ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከአንድ ሚልዮን በላይ ሰው ተገኝቷል መባሉ

ምን ተብሎ ነበር?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ሀላፊዎች በመስቀል አደባባይ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ እና ለደጋፊዎች ምስጋና በተደረገበት መርሐግብር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መታደማቸውን አስታውቀው ነበር። ኢቢሲን ጨምሮ አንዳንድ ሚዲያዎች ይህን ቁጥር ለዜና ግብዐትነት ተጠቅመውበት ነበር።

እውነታው ምን ነበር?

መስቀል አደባባይ አንድ ሚሊዮን ሰው የመያዝ አቅም የለውም። ኢትዮጵያ ቼክ ማፕ ቼኪንግ የተባለ መተግብሪያን በመጠቀም ባደረገው ልኬት አደባባዩ በጣም በተጠጋጋ ሰው አሰላል እንኳን ሊይዘው የሚችለው የሰው መጠን መቶ ሰማንያ አራት ሺህ አምስት መቶ ሰው ገደማ መሆኑን አረጋግጧል።

2. ሲ.ኤን.ኤን በግብዐትነት የተጠቀመው ተመሳስሎ የተከፈተ የትዊተር አካውንት

ምን ተብሎ ነበር?

መቀመጫውን በአትላንታ ጆርጅያ ያደረገው ታዋቂው የቴሌቪዥን ጣብያ ሲ.ኤን.ኤን (CNN) 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በሚደረግበት ቀን ማለዳ ‘Ethiopians head to the polls amid conflict and a raging humanitarian crisis’ በሚል ርዕስ ረዘም ያለ ጽሁፍ አስነብቦ ነበር። ሲ.ኤን.ኤን ለጽሁፉ በግብአትነት ከተጠቀመባቸው መረጃዎች መካከል የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ስምና ምስል በጠቀም በተከፈተ የትዊተር አካውንት ላይ የተለጠፉ ትዊቶች ይገኙባቸው ነበር።

እውነታው ምን ነበር?

ሲኤንኤን ለዜና ግብአትነት የተጠቀመበት የትዊተር አካውንትም ሆነ በአካውንቱ ላይ የሰፈረው መልዕክት ፕሮፌሰር መረራ አልነበረም። ኢትዮጵያ ቼክ ሲኤንኤን የሰራውን ስ ህተት ካጋለጠ በኃላ የቴሌቪዥን ጣብያው የዕርምት እርምጃ ወስዷል።

3. ኢትዮጵያን ሄራልድ የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት (USAID) በአክሱም ምርመራ ስለማድረጉ የሰራው ዘገባ

ምን ተብሎ ነበር?

ዕለታዊው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ኢትዮጵያን ሄራልድ በፊት ገጹ “የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት ባደረገው ምርመራ [በአክሱም] የቀብር ስፍራዎች እንዲሁም ተጎጂዎች እንደሌሉ አረጋገጠ” የሚል ዘገባ ሰርቶ ነበር።

እወነታው ምን ነበር?

የእርዳታ ድርጅቱ በአክሱም ምርመራ አላካሄደም፣ ወደ ስፍራውም ቡድን አልላከም በማለት ነበር። ኢትዮጵያ ቼክ መረጃውን ለማጣራት በወቅቱ የአሜሪካ ኢምባሲን አነጋግሮ ነበር።

4. ስናይፐር የጦር መሳሪያ ይዛ የታየችው ሴት ጉዳይ

ምን ተብሎ ነበር?

 ሞናሊዛ አብረሃ ስናይፐር መሳሪያ ይዛ የሚያሳይ ነው የተባለ ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በስፋት ተሰራጭቶ ነበር። በማዕከላዊ ትግራይ ዞን የተንቤን አካባቢ ተወላጅ የሆነችው ሞናሊዛ አብርሃ ህዳር 25፣ 2013 ዓ.ም የኤርትራ ወታደሮች ሊደፍሯት በሞከሩበት ወቅት እጇን በጥይት መመታቷን በመቀሌ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ለተገኙ የአልጀዚራ ዘጋቢዎች መናገሯ ይታወቃል። ከደረሰባት ጉዳት በኃላ እጇ እንዲቆረጥ መደረጉን ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጨምራ ገልጻ ነበር፣ ጉዳቷም በፕሮግራሙ ላይ ታይቷል።

እውነታው ምን ነበር?

ኢትዮጵያ ቼክ በተሰራጨው ምስል ላይ ባደረገው ማጣራት ስናይፐር መሳሪያ ይዛ በፎቶ የምትታየው ወጣት ሴት ሞናሊዛ አብረሃ አለመሆኗን አረጋግጧል። በርካቶች ሞናሊዛ አብርሀ እንደሆነች ገልፀው ሲለጥፉት የነበረው እና ስናይፐር መሳሪያ ይዛ በፎቶው የምትታየው ወጣት ዕለምለምዕ በሚል ስም የፌስቡክ አካውንት ያላት ግለሰብ ነበረች።

5. በዲፕ ፌክ (Deepfake) የተመረተ ፎቶ ተጠቃሚው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀድሞ ባልደረባ ጆርጅ ቦልተን 

ምን ተብሎ ነበር?

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ዋልታ ጆርጅ ቦልተን የተባሉ “የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ኃላፊ” በትዊተር ገጻቸው አስተላለፉ ያሉትን መልዕክት ለዜና ግብዐትነት ተጠቅመው ነበር። በዜናዎቹም “የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሽግግር ያደናቅፋል” ብለው እኚህ ግለሰብ እንደተናገሩ እነዚህ ሁለት ሚድያዎች ጠቅሰውም ነበር።

እውነታው ምን ነበር?

ኢትዮጵያ ቼክ በጆርጅ ቦልተን የትዊተር አካውንት ላይ ባደረገው ማጣራት የፕሮፋይል ምስሉ የረቀቀ የማስመሰል ጥበብን (deepfake) በመጠቀም የተሰራ ሀሰተኛ ፎቶ መሆኑንን አረጋግጧል። ከቀናት በኃላ የትዊተር አካውንቱ የፕሮፋይል ፎቶው በሌላ ተቀይሯል፣ ይሁንና የተቀየረው ፎቶ የአሜሪካዋ ግዛት ቴነሲ ገዢ በነበሩት ጆን ዊልደር ነበር። ከቆይታ በኃላ ኣአካውንቱ ተዘግቷል።

6. ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የምርጫ ቦርድ ሃላፊነታቸውን በመልቀቅ ወደ አሜሪካ ሊሄዱ ነው ተብሎ የተሰራጨ መረጃ

ምን ተብሎ ነበር?

በመስከረም ወር የመጀመሪያ ሳምንት የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ስልጣናቸውን ለቀው አሜሪካ ወዳገኙት አዲስ ስራ ሊያመሩ ነው የሚል መረጃ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።

እወንታው ምን ነበር?

የተሰራጨው መረጃ ሀሠት ነበር።

7. የኮቪድ-19 ክትባት መጀመሪያ የሚከተቡት የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው ተብሎ የተሰራጨ ዜና

ምን ተብሎ ነበር?

ሳምንታዊው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ጋዜጣ ካፒታል በፌስቡክ ገጹ እና በድረገጹ የኮቪድ-19 ክትባት በመጀመርያ የሚሰጠው ለመንግስት ሀላፊዎች ነው የሚል ዜና አስነብቦ ነበር።

እውነታው ምን ነበር?

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ቼክ የጤና ባለሙያዎች እና እድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑ ግለሰቦች በቅድሚያ ክትባቱ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል። አክለውም “ጥቂት የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የክትባቱ መጀመርን በማስመልከት እና ለሌሎችም አርአያ በመሆን ለማሳየት ሊከተቡ ይችላሉ፤ በአጠቃላይ ግን የመንግስት ሀላፊዎች የመጀመርያ ክትባት ያገኛሉ መባሉ ትክክል እንዳልሆነ” አስረድተዋል።

8. የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች እጩዎችን በሀይማኖት ለይቶ መዝግቧል ተብሎ የተሰራጨ መረጃ

ምን ተብሎ ነበር?

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ የሚሳተፉ እጩዎችን በሀይማኖት ለይቶ እንደመዘገበ የሚጠቁሙ መረጃዎች በተለይ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በስፋት ተሰራጭተው ነበር። አንዳንዶችም የእጩዎችን የሀይማኖት ስብጥር ዝርዝር ያሳያል ያሉትን መረጃ ከምርጫ ቦርድ እንዳገኙ በመጥቀስ መረጃ አጋርተው ነበር።

እውነታው ምን ነበር?

ቦርዱ የሚሰበስበው የእጩዎች ዝርዝር ላይ ምንም አይነት የሀይማኖት ስብጥርን የሚያሳይ መረጃ አይጠቀምም።

9. ዜግነት የሌላቸውን ኢትዮጵያዊንን ከሀገሯ ልታስወጣ ነው ተብሎ የተሰራጨ መረጃ

ምን ተብሎ ነበር?

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት አሜሪካዊ ዜግነት የሌላቸውን ማንኛውም ኢትዮጵያዊያን ከአገሯ እንዲወጡላት የሚያዝ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቷን የሚገልጽ ጽሁፍ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ተሰራጭቶ ነበር። የተሰራጨው ጽሁፍ አክሎም “[ረቂቁ] ለሕዝብ መወሰኛው የላይኛው ምክር ቤት መቅረቡን አንድ የአሜሪካን የፓርላማ ምክር ቤት አባል መናገራቸው በሰፊው እየተዘገበ ነው። ይህም ሰሞኑን በተፈጠረው የኢትዮጵያ መንግሥት ቅስቀሳ የአሜሪካን ባንዴራን እናቃጥላለን ማለታቸውን ተከትሎ ነው” በማለት አስነብቦ ነበር።

እውነታው ምን ነበር?

መረጃው ሙሉ በሙሉ ሀሠተኛ ነበር። ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ቢሮ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ቼክ  በሰጠን መልስ “እነዚህ ግርምትን የሚጭሩ የኦንላይን ሪፖርቶች ሙሉ በሙሉ የሀሰት ናቸው። እንዲህ አይነት የሀሰተኛ መረጃዎች በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ከማባባስ የዘለለ ፋይዳ የላቸውም” ብሏል።

10 በዚህ ዓመት የተነሳ ነው ተብሎ የተሰራጨ ፎቶ ጉዳይ

ምን ተብሎ ነበር?

በረሃብ የተጎሳቆለች ሴት ምስል የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በስፋት ተሰራጭቶ ነበር። ፎቶው በዚህ ዓመት በትግራይ ክልል የተነሳ ነው በሚሉና ኣአይ ኣአይደለም በሚሉ ወገኖች መካከልም ውዝግብ ፈጥሮ ነበር።

እውነታው ምን ነበር?

በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተከሰተው ረሀብ ወቅት የተነሳ ፎቶ ነው። ፎቶውን ያነሳው ጆን አይዛክ የተባለ የፎቶ ባለሙያ ሲሆን በወቅቱ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያነሳው ፎቶ እንደሆነ አረጋግጠናል። ግለሰቧ በርሀብ ምክንያት ክፉኛ ተጎድታ ህክምና ለመከታተል ወደ መቐለ ከተማ እንደመጣችም የፎቶው መግለጫ ያሳያል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::