ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ሰራተኞችን መላክ የሚችል ፈቃድ ያለው አንድም ተቋም እንደሌለ ተገለጸ! 

አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ወደ አውሮፓ ሀገራት ስራ እናስቀጥራለን የሚሉ ማስታወቂያዎች ሲሰሙ ይደመጣል። አንዳንዶቹም በግልጽ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ቢሮ ከፍተው ወደ ካናዳ፣ አሜሪካ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ስራ እናስቀጥራለን የሚሉ ማስታወቂያዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር ያሰማሉ። 

በቅርቡም ኢትዮጵያ ቼክ “ዋን ኮንሰልታንሲ” የተባለ ድርጅት እንቅስቃሴን ካጋለጠ በሗላ ቢሮው በፖሊስ እንደተዘጋ እና ምርመራ እንደተጀመረ አስነብበን ነበር። 

ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግም አል ዐይን አማርኛ ጉዳዩ ወደ ሚመለከተው አሁን ስሙ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም በቀድሞ ስሙ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴርን ጠይቋል። 

በዚህ ተቋም በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት የስራ ውል አጽዳቂ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ገሰሰ ደሬሳ እንዳሉት ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ሀገራት ስራ እናስቀጥራለን የሚሉ ማስታወቂያዎችን እና እሮሮዎችን እንደማንኛውም ሰው እንደሚሰሙ ተናግረዋል። 

ይሁንና በአዋጅ 923/2008 ዓ.ም መሰረት የውጭ ሀገራት ስምሪትን የሚያስፈጽመው የእሳቸው ተቋም መሆኑን ተናግረው እስካሁን መስፈርቱን አሟልቶ ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ሀገራት ሰረታኞችን መልምሎ መላክ የሚያስችል ፈቃድ ያለው ኤጀንሲ እስካሁን እንደሌለ ተናግረዋል። 

በመሆኑም ወደተጠቀሱት አህጉራት ሰረታኞችን ልከን ስራ እናስቀጥራለን በሚል የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ ኤጀንሲዎችን ህግ አስከባሪ የጸጥታ አካላት እንዲያስቆሟቸው አቶ ደሬሳ አሳስበዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም ዜጋ ለነዚህ ህገወጥ ኤጀንሲዎች ገንዘብ ከመክፈላቸው በፊት ህጋዊነታቸውን እንዲጠይቁ ተጨማሪ መረጃዎችንም ካዛንቺስ ወደሚገኘው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መጥተው እንዲያጣሩም አሳስበዋል። 

የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት አዋጅ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟላ እና ከዚህ ተቋም የስራ ፈቃድ ያገኘ ኤጀንሲ ወደማንኛውም ሀገር ሰራተኞችን መልምሎ እንዲልኩ ቢፈቅድም እስካሁን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውጭ ወደ ሌሎች ሀገራት እየተላከ አለመሆኑንም አቶ ገሰሰ ገልጸዋል። 

Via Al Ain Amharic

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::