የመኪና ባለቤትነት ስም ዝዉዉር ክፍያ ላይ ለዉጥ ተደርጓል?

ከሰሞኑ “ኮድ 3 መኪና ስም ለማዞር ሻጭ የመኪናዉን ግምት 35% እንዲሁም ገዢ 15% እንዲከፍሉ ተብሏል” በሚል የመረጃዉን ትክክለኛነት እንድናጣራ ከተከታዮቻችን ጥቆማ ደርሶናል።

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲሁም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት /የቀድሞ ዉልና ማስረጃ/ አናግሯል።

በአዲስ አበባ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጥና ፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ታዬ ዲባባ “እኛ ጋር ስም ዝዉዉር ነዉ። ከሰነዶች ማረጋገጫ ሽያጭ ዉሉ ሲመጣ የሊብሬ ብቻ ነዉ የምናስከፍለዉ እንጂ ምንም ክፍያ የለም” ብለዋል።

በተጨማሪም በተቋማቸዉ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ክፍያ ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ መሆኑንም ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

በሌላ በኩል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የሰነድ መመዝገብና ማረጋገጥ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ስለሺ ተቋማቸዉ ባሉት ቅርንጫፎች የመኪና ሻጭና ገዢን ዉል የማዋዋል ስራ እንደሚሰራ ይናገራሉ።

“ሻጭና ገዢ ማሟላት ያለባቸዉን እንዲያሟሉ አድርገን፤ ዉል አዋዉለን ዉሉ ላይ ይፈርማሉ። ከዛን እኛ አረጋግጠን መክፈል የሚገባቸዉን በጉምሩክ አዋጅ መሰረት ገዢዉ 2% ቀረጥ ገቢ ያደርጋል” ብለዋል።

በተጨማሪም አቶ ሰለሞን ስለሺ ስም ዝዉዉር በተመለከተ “ገዢ 35% እና ሻጭ 15%” በሚል ለሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የሚከፈል ክፍያ እንደሌለ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

“ህጉ የሚለዉ ገዢዉ እንዲከፍል ነዉ። በገዢዉ ስም የተገመተዉን ገንዘብ 2% እንዲከፍል ተደርጎ ነዉ እንዲረጋገጥ የሚደረገዉ እንጂ 35% የሚባል ከኛጋ የተያያዘ የለዉም” ብለዋል።

በተጨማሪም ገዢዉ ለሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የሚከፍለዉ ክፍያ ለኮድ 1፤2 እንዲሁም ኮድ 3 መኪኖች ተመሳሳይ 2% እንደሆነ አቶ ሰለሞን ነግረዉናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::