የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እዉነታዎችና የሚዲያዎች የተሳሳቱ ዘገባዎች!

በትላንትናዉ እለት የተካሄደዉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ስነ ስርዓት የበርካታ ሚዲያዎችን ሽፋን አግኝቷል።

ይሁን እንጂ የተለያዩ ሚዲያዎች ዘገባዎች የቁጥር ስህተቶችና ከመንግስት አካላት ሲሰጡ ከቆዩና በትላንትናዉ ፕሮግራም ላይ ከተነገሩ መረጃዎች ጋር የሚጋጩ እንደሆኑ ተመልክተናል።

ለምሳሌ አል ዐይን አማርኛ “የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚይዘዉ የዉሃ መጠን 17 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ነዉ” በማለት የሰራዉን ግራፊክስ በፌስቡክ ገጹ አጋርቷል። ኦቢኤን አፋን ኦሮሞ ደግሞ ግድቡ ሲጠናቀቅ 74 ሜትር ኪዩብ ዉሃ እንደሚይዝ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በትላንትናዉ እለት በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረዉ መረጃ መሰረት ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የዉሃ መጠን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ነዉ።

በሌላ በኩል የግድቡ ሃይል የማመንጨት አቅም በተመለከትም የሚጣረሱ ዘገባዎች ተሰርተዉ ተሰራጭተዋል።

ከነዚህ መካከል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “የግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል” ሲል ዘግቧል።

ይሁን እንጂ በትላንቱ ፕሮግራም ንግግር ያደረጉት ታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይልና በአመት 15 ሺህ 760 ጂጋ ዋት ሰዐት ኢነርጂ የማመንጨት አቅም እንዳለዉ ነዉ የተናገሩት።

በተጨማሪም ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከተሰራጩ አሳሳች መረጃዎች መካከል ኢትዮጵያዊያንና መንግስት ስላደረጉት የገንዘብ ድጋፍ ነዉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) “ኢትዮጵያዊያን እና መንግስት ያለምንም የውጭ እርዳታ ለግድቡ ግንባታ ከ1.65 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል” ሲል የግድቡ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮን ጠቅሶ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ ስራ አስኪያጁ በግድቡ ኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ስነ ስርዓት ላይ እስካሁን ድረስ ለግድቡ ግንባታ ከ163 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና ይህም ኢትዮጵያዊያንና መንግስት የተገኘ እንደሆነ ነዉ የተናገሩት።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::