ዘ ቴሌግራፍ በጠ/ሚር አብይ ንግግር ዙርያ የሰራው የተሳሳተ ዘገባ! 

የእንግሊዙ ዘ ቴሌግራፍ “የኢትዮጵያው ጠ/ሚር የእርዳታ ምግብ ወደሀገራቸው መግባቱን አስቆማለሁ ብለው ዛቱ” የሚል ዘገባ ትናንት ሰርቶ አስነብቧል። ሚድያው አክሎም ጠ/ሚሩ ይህንን ያሉት የአለም አቀፍ ጫናን ለመቀነስ አስበው እንደሆነ ፅፏል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ አጭር ማጣራት ያረገ ሲሆን ጠ/ሚር አብይ አህመድ በአማርኛ የተናገሩት ንግግር “… በደንብ ሰርተን ስንዴ የሚባል ነገር እንዳይገባ ካደረግን 70 ፐርሰንት የኢትዮጵያ ችግር ይራገፋል” የሚል እንደሆነ ተመልክቷል። ጠ/ሚሩ በዚሁ ንግግራቸው “ሁሉም የኢትዮጵያ ክልል በቀጣይ አመት የስንዴ ክላስተር 30 እና 40 ፐርሰንት ከተገበረ አንድ ኪሎ ስንዴ ኢትዮጵያ አይገባም” ብለው ነበር። 

ይህንንም ያሉት በቅርብ ቀናት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመሄድ የግብርና እንቅስቃሴዎችን በጎበኙበት ወቅት ነበር። 

ይህም በግልፅ እንደሚያሳየው “…ስንዴ የሚባል ነገር እንዳይገባ…” የሚለው አገላለፅ ራስን በምግብ ከመቻል ጋር ተያይዞ የቀረበ እንጂ የእርዳታ ምግብ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ለማድረግ ከመዛት ወይም ከማስፈራራት ጋር የተያያዘ አይደለም።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::