“የፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ ፖሊስ፣ የክልልና የፌዴራል የፍትሕ ተቋማት የሐሰተኛና ጥላቻ ንግግር ወንጀልን የሚፈጽሙ ሰዎችን ወደ ሕግ ማቅረብ አለባቸው”— የፍትሕ ሚኒስቴር 

የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ስብሰባ ሕዝብና ሀገርን ሰላም የሚነሡ ናቸው ባላቸው በሐሰተኛ መረጃ እና በጥላቻ ንግግር የሚሳተፉ አካላት ላይ አስፈላጊውን ሁሉ ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑ ተዘግቦ ነበር። 

ዛሬ ደግሞ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን እና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ከሁለት አመት በኋላም ይህን አሳሳቢ ተግባር የመከላከል ስራ በሚገባው ደረጃ እየፈጸመ አለመሆኑን የፍትህ ሚኒስቴርን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አንድ ዜና አስነብቧል። 

ከዚህ በኋላ የሀሰተኛ መረጃን በሚያሰራጩ ግለሰቦች ላይ በአዋጁ ላይ በተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች መሰረት ቅጣት እንደሚጣልባቸውም በዚሁ ዜና ላይ ተጠቅሷል። 

የፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ ፖሊስ፣ የክልልና የፌዴራል የፍትሕ ተቋማት የሐሰተኛና ጥላቻ ንግግር ወንጀልን የሚፈጽሙ ሰዎችን ወደ ሕግ ማቅረብ እንዳለባቸው በፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አወል ሱልጣን ተናግረዋል። 

“ይህን ማድረግ ባለመቻላችን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሰዎች ከመስመር ሲወጡና እንዲህ አይነት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ቆይተዋል” ብለዋል ዳይሬክተሩ። 

ሆን ተብሎ የሚሰራጩ የጥላቻና ሐሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከልከልና መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቅሰው ይህ አዋጅ፣ ሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ሁከትን የሚቀሰቅስ ወይም ብሔርን፤ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ በግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻ ወይም መድልዎ የሚያስፋፋ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ የማድረግ አላማ እንዳለውም ያብራራል። 

ይህን አዋጅ ተላልፎ መገኘት በወንጀል የሚያስቀጣ ሲሆን፣ እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም ከ100,000 ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ  እንደሚቀጣ በአዋጁ ተጠቅሷል። 

አዋጁ ሌሎች የመተላለፍ አይነቶችን ከነቅጣቸው በጥልቀት የሚዘረዝር ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ማህበራዊ ሚዲያን የተመለከተ ይገኝበታል። 

“የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሶስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከብር 100,000 ሺህ ያልበለጠ መቀጮ ይሆናል” ይላል ይህ የአዋጁ ክፍል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ስለአዋጁ የበለጠ መረዳት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ይጠቅማል ብሎ በጽኑ ያምናል። ከዚህ ጽሁፍ ስር ያለው ማስፈንጠርያ ወደ አዋጁ ሙሉ ይዘት ይወስደናል: https://www.article19.org/wp-content/uploads/2021/01/Hate-Speech-and-Disinformation-Prevention-and-Suppression-Proclamation.pdf

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::