በዋልታ “አሜሪካዊ” እንደሆኑ ተገልፆ የተሳሳተ ዜና የተሰራባቸው ግለሰብ!

ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል “የሳይበር ደኅንነት ስፔሻሊስትና የአሜሪካ የቀድሞው የመከላከያ መምሪያ የሥራ ኃላፊ ኦሊቨር ቶማስ” በትዊተር ገጻቸው አሰፈሯቸው ያላቸውን መልዕክቶች መሰረት በማድረግ ዛሬ ዘገባ ሰርቷል።

ዋልታ “አሜሪካዊው” ሲል የጠራቸው ግለሰብ ለትዊተር ገጻቸው የተጠቀሙትን የፕሮፉይል ፎቶና የትዊተር መልዕክታቸውን የስክሪን ቅጅ ከዘገባው ጋር አያይዟል።

ኢትዮጵያ ቼክ ዋልታ ለዘገባ ግብዓትነት የተጠቀመባቸው “ኦሊቨር ቶማስ” አሜሪካዊ ስለመሆናቸው ለማጣራት የትዊተር አካውንታቸውን በጥልቀት ተመልክቷል።

ከላይ የተጠቀሱት ግለሰብ እ.አ.አ በግንቦት ወር 2020 ዓ.ም ትዊተርን የተቀላቀሉ ሲሆን እስካሁን ከ2,120 ጊዜ በላይ መልዕክቶችን ለጥፈዋል እንዲሁም ግብረመልስ አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ ሁሉንም መልዕክቶችና ግብረመልሶች የተመለከተ ሲሆን፣ የአካውንቱ ባለቤት ቀደም ባሉት የትዊተር መልዕክቶቻቸው ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ እንደጻፉ አረጋግጧል።

ለምሳሌ ግለሰቡ እ.አ.አ ነሀሴ 17/2020 ዓም በጻፉት ትዊት ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በታህሳስ ወር ኢትዮጵያዊ መሆናቸውንና ወንድማቸው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ስለመሰዋቱ አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ ኦሊቨር ቶማስ ስለተባለው ግለሰብ እንዲሁም ስለሙያቸው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የድረ-ገጽ ዳሰሳ ያከናወነ ሲሆን በፎቶም ሆነ በሙያ ከሳቸው ጋር የሚመሳሰል ሰው ማግኘት አልቻለም።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ አንዳንድ ግለሰቦች ስማቸውን እንዲሁም ፎቷቸውን በተደጋጋሚ በመቀያየር ሌላ ማንነት ይዘው ሲቀርቡ በተደጋጋሚ መታየቱ ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::