በፍኖተ ሰላም ከተማ ዙርያ ተጋርቶ የነበረ መረጃ እና መሬት ላይ ያለው እውነታ!

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሚያዝያ 23/2014 ዓ.ም “የንጹኃን ዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታን መወጣት ያለመቻል የሥርዓቱ ውድቀት ማሳያ ነው!” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ በፍኖተ ሰላም ከተማ መስጊዶች መቃጠላቸውን የሚገልጽ መረጃ አጋርቶ ነበር። 

የኦፌኮ መግለጫን ተከትሎ የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት በከተማው “መስጊዶች ተቃጠሉ” ተብሎ የተሰራጨውን መረጃ ያስተባበለ ሲሆን በዛሬው ዕለት መረጃውን አሰራጭቷል ባለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ላይ “ተገቢውን የህግና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድልን” በማለት ለፌደራል የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ደብዳቤ መጻፉን ተመልክተናል። 

ኢትዮጵያ ቼክ የኦፌኮን መግለጫ እና የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤትን ደብዳቤ ከተመለከተ በሗላ ጉዳዩን ለማጣራት በፍኖተ ሰላም ከተማ “የመስጂደ-ሰላም” መሪዎችንና የከተማው ነዋሪዎችን አነጋግሯል። 

በፍኖተ ሰላም ከተማ የሚገኘው የመስጂደ-ሰላም መስጊድ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ዳውድ ሁሴን በከተማው በሚገኙ መስጊዶች ተቃጥለዋል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሀሠተኛ መሆን ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል። 

አቶ ዳውድ በከተማው አንድ ትልቅ መስጊድ እና አንድ አነስተኛ መስጊድ መኖሩን ገልጸው ምንም አይነት የቃጠሎም ሆነ ሌላ ችግር አለመከሰቱን አስረድተዋል። በትናንትናው ዕለትም የኢድ አልፈጥር በዓልን በማስመልከት በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የቡሬ ካምፓስ የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ ተማሪዎችን ወደ መስጊዱ ጋብዘው የምሳ ግብዣ ማደረጋቸው ገልጸዋል።  አቶ ዳውድ አክለው መንግስት ለእስላሙም፣ ለክርስቲያኑም ቤተ እምነት ጥበቃ ያድርግ ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በተጨማሪም በመስጊድ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ሁለት የከተማው ነዋሪዎችን እና አንድ ጋዜጠኛ ያነጋገረ ሲሆን ምንም የተፈጠረ ችግር አለመኖሩን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። 

ከሰሞኑ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሀይማኖት-ተኮር የሆኑ ብጥብጦች መከሰታቸውን በመንግስት እና የሀይማኖት አካላት የተገለፀ ሲሆን በዚህም የተወሰነ መስጊዶች እና ቤተክርስቲያኖች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተገልጿል። ኦፌኮ በመግለጫው ላይም በሌሎች ስፍራዎች እየደረሱ ናቸው ያላቸውን በርካታ ግጭቶች እና ጉዳቶች ዘርዝሯል። 

*** ኢትዮጵያ ቼክ ይህን መረጃ በማጣራት ላይ በነበረበት ሰዐት ኦፌኮ በፌስቡክ ገጹ ላይ አጋርቶት የነበረው መረጃን ማስተካከሉን አይተናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::