ትናንት በስፋት ተዘግቦ የነበረው “40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ሊገዛ ነው” ዜና ትክክል እንዳልሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል!

ካለፈው ሳምንት አንስቶ የተከሰተውን የምግብ ዘይት መጥፋትና የዋጋ መናር ችግሮችን ለመፍታት የ40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዥ ስምምነት አለመፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ጉዳዩ በጅምር ላይ ያለና ጥናት እየተካሄደበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ንግድ ቢሮዎች ጋር በመሆን ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተው የምግብ ዘይት ዋጋ መናር ለመፍታት የሚያግዝ 40 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

የሚኒስቴሩ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም ባህሩ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት እያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በልዩ ሁኔታ እንዲያስገቡ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረው ነበር፡፡

ዳይሬክተሯ መበደበኛ የግዥ ሒደቶችን መከተል ወራትን ሊወስድ ስለሚችል በልዩ ሁኔታ የሳዑዲ ዓረቢያ አስመጪ ድርጅት መመረጡንና ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ስምምነት መፈጸሙን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዓለም ላይ ያለው የምግብ ዘይት ዋጋ የሚታወቅ በመሆኑም አስመጪ ድርጅት መመረጡ ችግር እንደማይፈጥርም አክለዋል፡፡

ወ/ሮ መስከረም በጉዳዩ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ከሆኑት አቶ ኤፍሬም ተሰማ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ቢጠቁሙም፣ አማካሪው ከዚህ ተቃራኒ ነው የተናገሩት፡፡ እንደ አቶ ኤፍሬም ዘይት ለማቅረብ የተመረጠም ሆነ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ያደረገ አቅራቢ የለም፡፡ መንግሥት ሊያስገባ ያሰበው የዘይት መጠንን በተመለከተም፣ ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰና ጉዳዩ በጥናት ላይ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ምንጭ: ሪፖርተር ጋዜጣ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::